top of page

መጋቢት 20፣2016 - የሚፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መፍትሄ መስጠት ከመንግስት ይጠበቃል ተባለ

በኢትዮጵያ የሚፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መፍትሄ መስጠት ከመንግስት ይጠበቃል ተባለ፡፡

 

በኢትዮጵያ የማረሚያ ቤቶች አያያዝ ላለፉት 5 ዓመታት ከነበረው የሚሻል ቢሆንም መስተካከል የሚገባው ብዙ አለ ተብሏል፡፡

 

በኢትዮጵያ ባሉ ማረሚያ ቤቶች የህፃናትና የሴቶች አያያዝ አስከፊ ነው ተብሏል፡፡

 

ይህን ያለው ሴንተር ፎር ጀስቲስ የተባለ ተቋም በሀገሪቱ ባሉ ማረሚያ ቤቶች አደረግኩት ያለውን የክትትል ሪፖርት ይፋ ሲያደርግ ነው፡፡

 

የኢትዮጵያ መንግስት ባለፉት 5 አመታት እፈፅመዋለሁ ብሎ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጉባኤ ላይ በሚደረገው ሁሉን አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ግምገማ የተቀበላቸውን ምክረ ሀሳቦች አፈፃፀሙን የተመለከተ የሲቪል ማህበራት በተለያዩ የሰብአዊ መብት አያያዝ ሪፖርት ላይ ዛሬ ውይይት ተካሂዷል፡፡

 

በውይይቱ ላይ በሀገሪቱ የሚገኙ የተለያዩ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋማት በታራሚ አያያዝ፣ በሴቶች መብት እና በሌሎችም የሰብአዊ መብቶች ላይ ያተኮረ የክትትል ሪፖርት ይፋ አድርገዋል፡፡

 

የሴቶች መብት አያያዝን በተመለከተ ‘’ትምራን’’ የተሰኘ ሀገር በቀል ግብረ ሰናይ ድርጅት ባለፉት 5 አመታት ሴቶች ያላቸውን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ተሳትፎን የተመለከተ ሪፖርት አቅርቧል፡፡

 

በዚህም ባለፉት አምስት ዓመታት የሴቶች ተሳትፎ በፖለቲካውም በኢኮኖሚውም የተሻለ የነበረ ቢሆንም አሁን ግን መንሸራተት አሳይተዋል ተብሏል፡፡

 


ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን ሲመጡ የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ 51 በመቶ ደርሶ የነበረ ሲሆን አሁን ግን ወደ 22 በመቶ ወርዷል ሲባልም ሰምተናል፡፡

 

ይሁንና በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ ሴት ፕሬዚዳንት መኖሩ ይበል የሚያሰኝ ነው ተብሏል፡፡

 

ሴቶች ስራ አስፈፃሚ ተደርገው መሾማቸው ተገቢ ቢሆንም በስራ ቆይታቸው ውጤታማ ናቸው አይደለም የሚለውን ለመገምገም የስልጣን የጊዜ ቆይታቸው አጭር በመሆኑ አልተቻለም ሲባል ሰምተናል፡፡

 

በመድረኩ ላይ የሃይማኖት ነፃነትን የተመለከተ ሪፖርትም ቀርቧል፡፡

 

በሪፖርቱም ባለፉት 5 አመታት የሃይማኖት ተቋማት የየራሳቸው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ማቋቋማቸው በበጎ ጎን ተነስቷል፡፡

 

የሃይማኖት ተቋማት በግጭቶችና በተለያዩ ምክንያቶች መውደማቸውና ታሪካዊ ሀብታቸው መጥፋቱ ደግሞ በደካማ ጎን የተገመገመ ነው፡፡

 

 

ያሬድ እንዳሻው

 

 

የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

 

 

 

 

Comentarios


bottom of page