በዩኤስኤአይዲ ( #USAID ) የሚደረግለት የገንዘብ ድጋፍ በመቋረጡ ህልውናው አደጋ ላይ መውደቁን የኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ማህበር ተናገረ፡፡
በዚህም ምክንያት ከአጠቃላይ ሰራተኞቹ የግማሽ ያህሉን የስራ ውል ለማቋረጥ መገደዱንና ፕሮጀክቶችንም ማጠፉን ማህበሩ ነግሮናል፡፡
ላለፉት 59 ዓመታት በኢትዮጵያ የስነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎቶችን እየሰጠ የሚገኘው ቤተሰብ መምሪያ ማህበር፤ ባሉት 46 ክኒሊኮች፣ 529 በሚደርሱ ከመንግስት ጤና ተቋማት ጋር በአጋርነት እንዲሁም ከ428 የግል የጤና ተቋማት ጋር እየሰራ መሆኑን ነግሮናል፡፡
አቶ ጴጥሮስ ጌቼሬ በማህበሩ የክኒሊካል ሰርቪስ አገልግሎት ማናጀር ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት የአሜሪካ መንግስት የልማት ተራድዖ ድርጅት የሆነው USAID የቤተሰብ መምሪያ በርከት ያሉ ፕሮጀክቶች ሲደግፍ ቆይቷል፡፡

ይሁንና በቅርቡ ድርጅቱ በድንገት ድጋፉን ማቆሙን ተከትሎ በገንዘብ ይደግፋቸው የነበሩ 4 ትልልቅ #ፕሮጀክቶችን ለማቆም ተገድደናል ብለውናል፡፡
ህልውናውን አደጋ ላይ እስከመጣል ያደረሰው ምን ያህል ገንዘብ ቢያጣ ነው ስንል የጠየቅናቸው የማህበሩ የክኒሊካል ሰርቪስ አገልግሎት ማናጀር አቶ ጴጥሮስ ጌቼሬ ያጣነው የገንዘብ መጠንም ይሁን ከስራው ምን ያህሉ ተጎድቷል የሚለው ገና በጥናት የሚለይ ነው በማለት የተወሰኑ የሚታጠፉ ስራዎችን ይጠቅሳሉ፡፡
ምንም እንኳን በቁጥር ከመናገር ቢቆጠቡም የምንከፍለው በማጣታችን ከማህበሩ ሰራተኞች የግማሽ ያህሉን የስራ ውል ለማቋረጥ ተገድደናል ብለውናል፡፡
የፕሮጀክቶቹ መቋረጥ በብዙ ሺህዎች ለሚቆጠሩ ወጣቶች ይሰጥ የነበረውን የስነ ተዋልዶ ትምህርትና ህክምና እንዳንሰጥ አድርጎናል የሚሉት ሃላፊው የተቋረጡትን ፕሮጀክቶች ለመቀጠል ማህበሩ ወደ ሌሎች ረጂ ተቋማት እያማተረ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡
በዘላቂነት ከገባበት ችግር ለመውጣት ከመንግስት አካላት፣ ከሌሎች ረጂ ድርጅቶች ጋር ማህበሩ እየመከረ መሆኑን ሰምተናል፡፡
ምንታምር ፀጋው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 YouTube: https://tinyurl.com/ky57kspd
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
📌 Linkedin : https://tinyurl.com/yhycs5r
Comments