መጋቢት 2 2017 - ለእርሻ ስራ አስፈላጊ የሆነውና በመደበኛ የሚጠበቀው የበልግ ወቅት ዝናብ ሁኔታ እየተጠናከረ እንደሚሄድ ተነገረ።
- sheger1021fm
- Mar 11
- 1 min read
ለእርሻ ስራ አስፈላጊ የሆነውና በመደበኛ የሚጠበቀው የበልግ ወቅት ዝናብ ሁኔታ እየተጠናከረ እንደሚሄድ ተነገረ።
በሌላ በኩል አዲስ አበባን ጨምሮ አንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከፍተኛ የሙቀት መጠን እንደሚኖራቸው የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ተናግሯል።
ከየካቲት እስከ ግንቦት ያሉትን ወራት በሚጠቃለለው የበልጉ ወቅት ባለፉት 10 ቀናት ከቀላል እስከ ከባድ የዝናብ መጠን መመዝገቡንና ይህም በተለይ ለእርሻ ስራ አመቺ መሆኑን የነገሩን በኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የሚቲዮሮሎጂ ትንበያና ምክር አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አሳምነው ተሾመ(ዶ/ር ) ናቸው።

እስካሁን የተመዘገበው የዝናብ መጠን ለበልግ ወቅት አብቃይ አካባቢዎች የተመቸ እንደነበረና በመጪዎቹ አስር ቀናት የሚጠበቀው የዝናብ መጠን ለተፋሰሶች ውሃ የመያዝ መጠን እንዲሁም ለሰውና እንስሳት የመጠጥ ውሃ አቅርቦት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ዶክተር አሳምነው ነግረውናል።
በሌላ በኩል አዲስ አበባን ጨምሮ በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከሚኖረው ከፍተኛ የፀሀይ ሀይል ጋር ተያይዞ የቀኑ ከፍተኛ ሙቀት ከ35-40 ዲግሪ ሴልሽየስ ሊያሻቅብ እንደሚችልም የትንበያና ምክር አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ዶክተር አሳምነው ተናግረዋል።
የበልግ ወቅት ገና እየጀመረ በመሆኑም አሁን ከተመዘገበውና በመጪዎቹ አስር ቀናት ከሚጠበቀው የዝናብ ሁኔታ ከመጠን በላይ በሆነ ዝናብም ሆነ ሙቀት አስጊ የአየር ፀባይ የለም ተብሏል።
ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ…
ምህረት ስዩም
Comments