መጋቢት 15 2017 - ወደቀያቸው የተመለሱ የአላማጣ ወረዳዎች ነዋሪዎች አሁንም አስፈላጊው ድጋፍ እየቀረበላቸው አይደለም ተባለ፡፡
- sheger1021fm
- Mar 24
- 1 min read
ባሳለፍነው ክረምት ወደቀያቸው የተመለሱ የአላማጣ ወረዳዎች ነዋሪዎች አሁንም አስፈላጊው ድጋፍ እየቀረበላቸው አይደለም ተባለ፡፡
ከ53,000 በላይ የሚሆኑና ከ6 ወረዳዎች ተፈናቅለው በትግራይ ክልል ተጠልለው የቆዩ ነዋሪዎች ወደ ቀድሞ ቀያዬው መመለሳቸው ይታወሳል፡፡
የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደርና የፌዴራሉ መንግስት ባደረጉት #ተፈናቃዮችን የመመለስ ስራ ከተመለሱ ወደ ስምንት ወር ገደማ የሆናቸው ተፈናቃዮች አሁንም ምንም አይነት የማቋቋሚያ ድጋፍ እየተደረገላቸው እንዳልሆነ ሰምተናል፡፡
ምንም አይነት ድጋፍ ባይቀርብላቸውም ከዚህ ቀደም ከሚኖሩት ማበረሰብ ጋር በሰላም መኖራቸው ትልቅ እድል ነው ሲሉ የተናገሩት የጊዜያዊ አስተዳደሩ ደቡብ ትግራይ ብሎ በሚጠራው አካባቢ አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ሀብቱ ኪሮስ ናቸው፡፡
የሰላምና የጋራ ጉዳዮችን እንዲመካከሩ እና እንዲሰሩም እድል ፈጥሯል ሲሉ አቶ ኪሮስ አስረድተዋል፡፡

የትግራይ ክልል ጊዜአዊ አስተዳደር ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ገብረሂወት ገ/እግዚአብሄር(ዶ/ር) ዓለም ዓቀፍ ረጂ ተቋማት ድጋፍ በማቋረጣቸው አይደለም የተመለሱት በመጠለያ ያሉትም ከየካቲት ወር ጀምሮ ድጋፍ እንዳላገኙ ነግረውናል፡፡
የፌዴራሉ መንግስት ለእነዚህ ወደ መኖሪያ ቀዪአቸው ለተመለሱ እና ድጋፍ ለመጠበቅ ለተገደዱ ሰዎች ድጋፍ እየሰጠ ነው ወይ ብለን ጠይቀናል፡፡
የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ባለሞያ ''የትግራይ ክልል ችግሩ ከአቅሜ በላይ ነው ድጋፍ ይደረግልኝ ብሎ አልጠየቀኝም ስለዚህም ድጋፍ አልላኩም'' የሚል መልስ ሰጥተዋል፡፡
አቶ ኪሮስ በበኩላቸው ሀላፊነቱ የራሱ የፌዴራሉ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ነው ብለዋል፡፡
ማርታ በቀለ
Comments