top of page

መጋቢት 13፣2016 - በዓለም ዙሪያ ከውሃ ጋር በተገናኘ የሚፈጠር ግጭት ባለፉት አስር ዓመታት መጠኑ በሶስት እጥፍ ጨምሯል ተባለ

በዓለም ዙሪያ ከ 3 ቢሊዮን በላይ ህዝብ በድንበር ተሻጋሪ የውሃ ሀብት ላይ ጥገኛ መሆኑ ተነግሯል።

 

ውስን የሆነውን የውሃ ሀብት መጠበቅና በወጉ መጠቀም ካልተቻለ የግጭት መነሻ ይሆናል ተብሏል።

 

ኢትዮጵያን ጨምሮ በዓለም ዙሪያ ብዙ ሀገራት ድንበር ተሻጋሪ የውሃ ሀብት ቢኖራቸውም የትብብር ማእቀፍ ያላቸው ግን 24ቱ ብቻ መሆናቸው ተነግሯል።

 

ይህ ሀሳብ የተነሳው ዓለም አቀፍ የውሃ ቀን ዛሬ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሲከበር ነው።

 

የዛሬው እለት ዓለም አቀፍ የውሃ ቀን ተብሎ በውሃ ሀብትና አጠቃቀም ዙሪያ የሚመከርበት ሲሆን ውሃን ለሰላም እንዴት መጠቀም ይቻላል በሚል ሀሳብ እለቱ በዓለም ዙሪያ እየተከበረ ነው።

 

በዝግጅቱ ላይ ሲነገር እንደሰማነው በዓለም ዙሪያ ውስን የሆነው የውሃ ሀብት የግጭትና አለመግባባት ምክንያት እየሆነ ነው።

 

አስራ ሁለት ተፋሰሶች ያላት ኢትዮጵያም ከ75  በመቶ በላይ ተፋሰሶቿ ድንበር ተሻጋሪ ናቸው ተብሏል።

 

ኢትዮጵያ በድንበር ተሻጋሪ የውሃ ሀብቷ ዙሪያ ውሃውን ከሚጋሩ ሀገራት ጋር በጋራ በመጠቀምና በመንከባከብ ዙሪያ የትብብር ማእቀፍ ሊኖራት ይገባል ተብሏል።

 

የቀደሙ የቅኝ ግዛት ስምምነቶች ኢትዮጵያ የተፋሰሶች መነሻ ብትሆንም ድርሻውን ለተቀሩት ሀገራት የሚሰጥ ነው ያሉት በዝግጅቱ ላይ ፅሁፍ ያቀረቡ ባለሙያዎች ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ የትብብር ማእቀፍ እንዲኖር ኢትዮጵያ ግፊት እያደረገች ነው ብለዋል።

 

በዓለም ዙሪያ ከ 3 ቢሊየን በላይ ህዝብ የድንበር ተሻጋሪ ውሃ ጥገኛ ሲሆን ወደ 276 ድንበር ተሻጋሪ ተፋሰሶች መኖራቸውም ተነግሯል።

 

የትብብር ማእቀፍ ያላቸው ግን 24 ሀገራት ብቻ ናቸው ተብሏል።

 

የውሃ እጥረትና ብክለት እንዲሁም ፍትሀዊ ያልሆነ ድርሻ የግጭት መነሻ እየሆነ ስለመምጣቱ የተነገረ ሲሆን ባለፉት አስር ዓመታትም በውሃ ምክንያት የሚነሳው ግጭት በሶስት እጥፍ መጨመሩ ተነግሯል።

 

በዓለም ባንክ የ 2022 ሪፖርት መሰረትም በዓለም ዙሪያ ከሚደርስ የተፈጥሮ አደጋ ሞት ፣ ከውሃ ጋር በተገናኘ የሚደርሰው ከአጠቃላዩ ሰባ በመቶ ድርሻ አለው።

 

ይህም የውሃን ነገር በህግ ማእቀፍ መምራት፣ውስን የሆነውን የውሃ ሀብት በትብብር መጠበቅ እንደሚገባ የሚያሳይ ነው ተብሏል።

የአየር ንብረት ለውጥና የህዝብ ቁጥር መጨመር  ችግሩን የበለጠ አሳሳቢ እያደረገው መምጣቱም ተነግሯል።

 

እለቱን ውሃን ለሰላም በሚል ሀሳብ ማክበር ያስፈለገውም በዚሁ ምክንያት ነው ተብሏል።

 

በተባበሩት መንግታት የህፃናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ እና በዓለም የጤና ድርጅት የ2023 ሪፖርት፣ በዓለም ዙሪያ 2.2 ቢሊየን ህዝብ ደህንነቱ የተጠበቀ የመጠጥ ውሃን አያገኝም።

 

 

ቴዎድሮስ ወርቁ

 

የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

 

 

 

 

Comments


bottom of page