በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ የተፈጠረዉ ክስተት የሳይበር ጥቃት አለመሆኑን አረጋግጫለሁ ሲል የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ተናገረ።
ያጋጠመው ከሲስተም ማሻሻያ ትግበራ ጋር በተያያዘ የተፈጠረ እንጂ የሳይበር ጥቃት መሆኑን የሚያሳይ መረጃ አለመገኘቱን አስተዳደሩ ጋዜጠኞችን ጠርቶ ተናግሯል።
የአስተዳደሩ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ መስሪያ ቤታቸው ባደረገዉ ምርመራ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከውስጥም ይሁን ከውጭ ለሚቃጡበት የሳይበር ጥቃቶች አስቀድሞ መከላከል የሚያስችል አቅም እንዳለዉና አስፈላጊውን የሳይበር ደህንነት ጥንቃቄ እንደሚያደርግ በባንኩ ሲስተሞች ላይ የተደረገዉ ፍተሻ እንደሚያሳይ ተናግረዋል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ባደረገው የደህንነት ፍተሻና ምርምራ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ የተፈጠረዉ የሲስተም ችግር የሳይበር ጥቃት ምክንያት መሆኑን የሚያሳይ ምንም ዓይነት መረጃ አለመገኘቱን ወ/ሮ ትዕግስት አስረድተዋል።
ነገር ግን ችግሩ እንዲከሰት ምክንያት የሆኑ ጉዳዮች በምርመራ የትለዩ ሲሆን ይህም ባንኩ በሞባይል ሲስተሙ ላይ ባደረገዉ የማሻሻያ ሥራ የተከሰተ መሆኑን ዳይሬክተሯ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሲስተም ማሻሻያ በሚደረግበት ወቅት ቀደም ብሎ ሌላ ሲስተም ማለትም T24 (ኮር ባንኪንግ ሲስተም) ጥቅም ላይ የዋለ የስሌት ሞጁል ወይም አልጎሪዝም በመውሰድ በሞባይል ባንኪንግ ሲስተሙ ላይ በቀጥታ ለመተግበር በተረገ ሙከራ ችግሩ መከሰቱን ሲነገር ሰምተናል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ባደረገው ምርመራ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሲስተም ጃር ፋይል ሶርስ ኮድ (JAR Files Source Code) ወስዶ ባደረገዉ ምርመራና ትንተና የፕሮግራሚንግ ቅደም ተከተሉ ወይም ሎጂካል ፍሰቱ የተዛባ ሆኖ በመገኘቱ ነው ተብሏል፡፡
አስተዳደሩ ተጨማሪ ምርመራዎች እና የፎረንሲክ ስራዎችን በማከናወን ውጤቱን ለሕብረተሰቡ ይፋ እንደሚደረግም የአስተዳደሩ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ ተናግረዋል።
ፍቅሩ አምባቸው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Telegram: https://tinyurl.com/yc6tfzsw
Website: https://www.shegerfm.com/
Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Comments