top of page

መጋቢት 12 2017 - የኤልሣቤጥ ወልደጊዮርጊስ (ዶ/ር) የቀብር ስነ ስርዓት ተፈጸመ

  • sheger1021fm
  • Mar 21
  • 3 min read

የኤልሣቤጥ ወልደጊዮርጊስ (ዶ/ር) የቀብር ስነ ስርዓት ተፈጸመ፡፡


የኤልሣቤጥ የቀብር ስነሥርዓት(ዶ/ር) የተፈጸመው በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሲሆን ከዚያ ቀደም ብሎ በአዲስ አበባ ዪኒቨርሲቲ ራስ መኮንን አዳራሽ የሽኝት ፕሮግራም ተካሂዷል፡፡


በሽኝት መርሃግብሩ ላይ የሙያ እና የሥራ ባልደረቦችዋ፣ ወዳጆቿ፣ ጓደኞቿ፣ ዘመድ እና የሥራዎቿ አድናቂዎች ተገኝተዋል፡፡


ኤልሣቤጥ ወልደጊዮርጊስ (ዶ/ር) ላለፉት አራት ዓመታት ሲያስተምሩበት እና ይኖሩበት በነበረው የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ሻርጃ ከተማ በድንገት ታመው ሆስፒታል በመግባት የህክምና እርዳታ ሲደረግላቸው ቆይቶ መጋቢት 07 ቀን 2017 ዓ.ም. በ69 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው ይታወሳል።

ከዛሬ 24 ዓመታት በፊት በ #አልቃይዳ የሽብር ጥቃት የኒዮርኮቹ መንትያ ህንጻዎች ሲወድሙ በህንጻው ውስጥ ከነበሩና በህይወት ከተረፉት መካከል አንዷ የሆኑት ዶ/ር አልሳቤጥ የተወለዱት ግንቦት 1 ቀን 1948 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሲሆን የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በናዝሬት ት/ቤት ነው፡፡


የከፍተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በአሜሪካ ከሞርጋን ስቴት ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ተከታትለው በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቀዋል።


በተማሩበት ሙያ ለዓመታት እዚያው በአሜሪካ ሀገር በተለያዩ ባንኮች ውስጥ በተለያዩ ደረጃዎች ማገልገላቸውን ዛሬ በሽኝታቸው ላይ የተነበበው የህይወት ታሪካቸው ያስረዳል።


ዶ/ር ኤልሳቤጥ በተለይ ለ #ሥነ_ጥበብ እና ለታሪክ በነበራቸው ልዩ ዝንባሌ፤ እንዲሁም እስክንድር ቦጎስያንን ከመሳሰሉ ሰዓሊዎች እና የጥበቡ ማህበረሰብ ጋር በነበራቸው የጠበቀ ወዳጅነት ወደ ጥበብ በመሳብ የድኅረ ምረቃ ትምህርታቸውን ከኒው ዮርክ ዩኒቨርሲቲ በሙዝየም ጥናት፣ ዶክትሬታቸውን ደግሞ በሥነ ጥበብ ታሪክ እና ሂስ ከኮርኔል ዩኒቨርሲቲ በ2000 ዓ.ም ተቀብለዋል።

ለዶክትሬት የመመረቂያ ጽሑፍ ዘመናዊነት እና የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሥነ-ጥበብ ታሪክ ላይ በማተኮር ያካኼዱት ጥናት እና ምርምር ( #Modernist_Art_In_Ethiopia ) በሚል ስያሜ በኦሀዮ ዪኒቨርሲቲ ፕሬስ እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ ለታተመው መጽሐፋቸው ዋነኛው እርሾ ነበር።


ዶ/ር ኤልሣቤጥ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናት እና ምርምር ተቋምን የመምራት ኃላፊነት ተረክበው ከ1996 እስከ 2002 ዓ.ም በዳይሬክተርነት አገልግለዋል።


በመቀጠልም በዩኒቨርሲቲው የቴአያትር ጥበባት፣ የያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት እና የአለ ሥነ - ጥበብና ዲዛይን ት/ቤት ተቀናጅተው "እስክንድር ቦጎስያን የክወና እና የዕይታ ጥበባት ኮሌጅ" እንዲቋቋም በማስቻል ኮሌጁ ከተመሠረተበት ከ2001 እስከ 2004 ዓ.ም በዲንነት አገልግለዋል።

በተጨማሪም በአለ የሥነ-ጥበብና ዲዛይን ት/ቤት የፊልም እና የሥነ-ጥበብ ድኅረ ምረቃ ትምህርት ክፍልን በማቋቋም ሂደት የበኩላቸውን ሚና የተጫወቱት ዶ/ር ኤልሳቤጥ በዚሁ ትምህርት ክፍል በማስተማር፤ የተማሪዎቻቸውን የሥነ-ጥበብ እሳቤ፣ እውቀት እና ልምምድ እንዲዳብር የነበራቸው አስተዋጽዖ ከልዩ ሙያዊ አበርክቶዎቿ አንዱ ነው፡፡


ለኢትዮጵያ ብቸኛ የሆነው የዘመናዊ ሥነ - ጥበብ ቤተ-መዘክር #ገብረ_ክርስቶስ_ደስታ_ማዕከል መስራቾች አንዷ በመሆን ቤተ-መዘክሩ ከተቋቋመበት ከመስከረም 2001 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ዙሮች ሁለት ጊዜ በዳይሬክተርነት መርተዋል።

በዚህ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ዕውቅና ያካበቱትን የትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ጁሊ ምህረቱን እና ዴንማርካዊ አይስላንዳዊውን ኦላፉር ኤልያሰንን ጨምሮ ስመጥር የሀገራችንን ሠዓልያን ሥራዎች ጭምር ለህዝብ ዕይታ አቅርበዋል።


ዶ/ር ኤልሳቤጥ በሸገር ኤፍ. ኤም 102.1 ሬዲዮ ሸገር ካፌ ፕሮግራም የዳበረ ዕውቀት እና ልምዳቸወን ለዓመታት በተከታታይ በተለያዩ ርዕሶች ዙሪያ ጥልቅ ውይይቶችን በማዘጋጀት፣ በመምራትና በመሳተፍ አሰተዋፅዎ አድርገዋል።


የዘመናዊነት እና የዘመናዊ ሥነ-ጥበብ ጽንሰ ሃሳቦችን፣ ያለፈውን እና የአሁን ዘመን የስነጽሁፍ ስራዎችን፣ የፓን አፍሪካ ተጋድሎዎች እና #የኢትዮጵያ_ታሪክ መዛግብትን ከአለም ዐቀፍ ጥናቶች ጋር በማጣቀስ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተወስነው የነበሩ የፍልስፍና እና የጥበብ ጽንሰ ሃሰቦችን ላይ ሃሰብ በማቅረብ፣ ውይይት አንዲደርግባቸው ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡

ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ በተባበሩት ዐረብ ኤሜሬትስ ሻርጃ ከተማ በዓለም ዓቀፍ ጥናት ዩኒቨርኒቲ (Global Studies University) የአፍሪካ ኢንስቲትዩት የአሊ መዝሩዊ ቀዳሚ ከፍተኛ ፌሎው በመሆን ተቀላቅለዋል፡፡


በተቋሙ የድኅረ-ምረቃ እና የዶክትሬት ትምህርት ክፍል የመሰረቱ ሲሆን በተጓዳኝ የሂውማኒቲስን ትምሀርት ክፍል በመምራት፣ ካሪኩለም በመቅረፅና በማስተማር አዲስ ለተከፈቱት የትምህርት መርሃ ግብሮች በድንገት እስካለፉበት ቀን ድረስ በተቋሙ የተለያዩ ጉባኤዎችና የሥነ-ጥበብ ዝግጅቶች፤ ኢትዮጵያውያን ምሁራን ተወዳዳሪ ሆነው ጥናት እንዲያቀርቡና አንዲያሳትሙ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከታቸው ይጠቀሳል፡፡


ዶ/ር ኤልሳቤጥ በእነዚህ ዓመታትም ያለማቋረጥ የጥናትና ምርምር ጽሑፎችን በአካዳሚክ መፅሄቶችና መጽሐፎች ላይ አሳትመዋል።


ዶ/ር ኤልሳቤጥ በመጨረሻ የህወት ዘመናቸው ወቅት ወዳጃውና ተስተካካይ የሌለው ምሁር ብለው የሚያምኑት የፕሮፌሰር አንድሪያስ እሼቴ ህልፈት፣ ከልጅነት አስከ እውቅት ያደጉበት መኖሪያ ቤታቸው በኮሪደር ልማት ምክንያት መፍረስ ያሳዝናቸው አና ይረብሻቸው እንደነበር በቅርበት የሚያውቋቸው ሲነገሩ ሰምተናል፡፡


ንጋቱ ሙሉ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…






Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page