መጋቢት 12 2017 - የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ወጋገን ባንክ በኢትዮጵያ የመጀመርያው የኢንቨስትመንት ባንክ ፈቃድ አገኙ
- sheger1021fm
- Mar 21
- 1 min read
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ወጋገን ባንክ በኢትዮጵያ የመጀመርያው የኢንቨስትመንት ባንክ ፈቃድ አገኙ።
ሲቢኢ ካፒታል አክሲዮን ኢንቨስትመንት ባንክ እና ወጋገን ካፒታል አክሲዮን ማህበር ኢንቨስትመንት ባንክ ፈቃድ ያገኙት የመጀመርያው የኢንቨስትመንት ባንኮች ናቸው።
እነዚህ ባንኮች እራሳቸውን ችለው የተቋቋሙ የካፒታል ገበያ ስራ ብቻ የሚሰሩ የኢንቨስትመንት ባንኮች ናቸው።
በተጨማሪም ለአምስት የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጭዎች ፈቃድ ተሰጥቷል።
ፈቃድ የተሰጣቸው አገልግሎት ሰጪዎች ህጉ የሚጠይቃቸውን መስፈርቶችና መመዘኛዎች አሟልተዋል ተብሏል።
ይህንን ፈቃድ አስመልክቶ ዛሬ የኢትዮዽያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ እና የካፒታል ገበያ ባለስልጣን ቦርድ ሰብሳቢ ማሞ ምህረቱ አብስረዋል።

የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ ገበያው የሀገሪቱን የክፍያ ሚዛን ያረጋጋል ከውጭ ብድር ጥገኝነትና የውጭ ብድር በመቀነስ የማክሮ ኢኮኖሚ ማረጋጋትን ይፈጥራል ብለዋል።
ታማኝነት ያለው የፋይናነስ ሥርዓት ለመገንባት የተዘረጋው የካፒታል ገበያ፤ ለማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋት ለመፍጠር ያግዛል ተብሏል።
ገበያው አዲስ እንደመሆኑ መጠን ለመቆጣጠር ብቻ ሳይሆን ከሚመለከታቸው ጋር አብሮ ለመስራት እድል መፈጠሩ ተነግሯል።
የኢንቨስትመንት ባንኮችና የሰነደ ሙአለ ነዋይ ኢንቨስትመንት አማካሪዎችን ጨምሮ ዛሬ ፈቃድ ያገኙ የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪዎች በድምሩ ዘጠኝ ደርሰዋል።
የኢትዮዽያ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሀና ተኸልቁ ዛሬ ፈቃድ የተሰጣችሁ በሙሉ ስራችሁ ሀላፊነት የተጣለበት በመሆኑ ህጉን አክብራችሁ እንድትሰሩ ሲሉ አሳስበዋል።
እነዚህ የኢንቨስትመንት ባንኮች ከንግድ ባንኮች የሚለዩ ሲሆን ቁጠባን አያሰባስቡም፤ ብድር አይሰጡም።
በምትኩ ኢንቨስትመንትን በማማከር በሌሎች የካፒታል ገበያ ስራዎች መሳተፍ እንደሚችሉ ሰምተናል።
ተህቦ ንጉሴ
Comments