top of page

መጋቢት 10 2017 - ጤናማና ዘላቂ የአመጋገብ ሥርዓትን ለማበጀት ያቀደ ''ኢኮ ፉድ ሲስተም'' የተሰኘ ፕሮግራም ይፋ ተደረገ

  • sheger1021fm
  • Mar 19
  • 1 min read

ሳይንሳዊ ጥናትን መሰረት አድርጎ ጤናማ እና ዘላቂ የአመጋገብ ሥርዓትን ለማበጀት ያቀደ ኢኮ ፉድ ሲስተም የተሰኘ ፕሮግራም ይፋ ተደረገ።

 

ፕሮግራሙ በአዲስ አበባ ያለውን የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እንዲሁም ላላስፈላጊ ውፍረት የሚዳርገውን ከመጠን በላይ የሆነ የአመጋገብ ሥርዓትን የሚያጠና ነው ተብሎለታል።

በተጨማሪም የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትላቸው ተፅዕኖዎችን እና የተለያዩ ችግሮችን መቋቋም የሚችሉ የምግብ ስርዓትን ለማቅረብ ያለመ መሆኑ የተነገረለት ይህ ፕሮግራም የአዲስ አበባ ነዋሪን በቀጥታ ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሏል።

 

ፕሮግራሙ በከተሞች ላይ ያለው የስርዓተ ምግብ ምን ሁኔታ ላይ ነው፣ ምንስ መስተካከል አለበት የሚሉ እና ሌሎች ጥናቶችም እየከወነ ለፖሊሲ አውጭዎች እና ለሚመለከታቸው ተቋማት መረጃ የመስጠት ስራ ላይ ትኩረቱን አድርጎ ይሰራል ተብሏል።

 

በከተማዎች ላይ ያለን የስርአተ ምግብ ሁኔታን እየተከታተሉ መረጃ መሰብሰብ ላይ በትኩረት ይሰራል የሚሉት በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት የስነ ምግብ እና የአካባቢ ጤና ዳይሬክተር ዶክተር ማስረሻ ተሰማ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ስርዓተ ምግብ ምን ደረጃ ላይ ነው፣ ምንስ ሊስተካከል ይገባል የሚሉና ተያያዥ ሀሳቦች ላይ ጥናት ይከውናል ብለዋል።

በአዲስ አበባ የምግብ ስርዓት ውስጥ ያለውን የተመጣጠነ ምግብ እጥረት በዘላቂነት ለመፍታት ይሰራል የተባለለት ይህ ፕሮጀክት ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በአጋርነት የሚከወን እና በጋልዌይ ዩኒቨርሲቲ የሚመራ መሆኑን ሰምተናል።

 

በአውሮፓ ህብረት እና በአለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ የገንዘብ ደጋፍ የተደረገለት መሆኑ የተነገረ ሲሆን በተለይ በአዲስ አበባ ጤናማ፣ ዘላቂ እና በተመጣጣኝ ዋጋ ሊገኙ የሚችሉ ምግቦች አቅርቦት ዙሪያ ለመስራት አቅዷል።

 

ፕሮጀክቱ ወደ ተግባር ሲገባም በአዲስ አበባ እየታየ ያለውን የስርዓተ ምግብ መጓደል ያስተካክላል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ሲሆን በቀጣዮቹ አመታትም ወደ ሌሎች ከተሞች የሚስፋፋ ነው ተብሏል።

 

ፋሲካ ሙሉወርቅ

 

የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

 

 

 

 

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page