ከአድዋ መታሰቢያ ሙዚየም ፊት ለፊት ካለው በተለምዶ የዶሮ ማነቂያ ተብሎ ከሚጠራው ሰፈር እስካሁን 1,600 አካባቢ አባዎራዎችን ማንሳቱን የአራዳ ክፍለ ከተማ ተናገረ፡፡
የአካባቢው የልማት ተነሺዎች በበኩላቸው መጀመሪያ ከፍለ ከተማው ሰብስቦን የሶስት ወር ቀነ ገደብ ሰጥቶን ነበር ፤ ከዚያም አስር ቀን ባልሞላው ውስጥ የሶስት ቀነ ገደብ ሰጥተውን አፈረሱብን የሚል ቅሬታ ለሸገር ነግረዋል፡፡
ኤርሚያስ የተባሉ ቅሬታ አቅራቢ የተሰጠን ምትክ ቦታ ቀድሞ ከነበርንበት የራቀ በመሆኑ ማህበራዊ ሕይወታችን ተበትኗል፤ የንግድ እና መኖሪያ ቤቶቻችንም ፈርሰዋል፤ በዚህም ስራ አቁመናል፤ የቀን ገቢያችንም፤ ተቋርጧል ሲሉ ቅሬታቸውን አቅርበዋል፡፡
ልጆቻችንም አሁን ከተሰጠን የመኖሪያ ቦታ ማለትም ከሃና ፉሪ አምጥተን ፒያሳ ለማስተማር ለአንድ ልጅ ያውም በባስ 30 ብር ይፈጃል በዚህ ላይ ስራ አቁመናል የተሰጠን መኖሪያ ቤትም መሰረተ ልማቱ የተሟላ አይደለም ይህ እንዴት ይቻለናል? ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
ለጥያቄዎቹ ምላሽ የሰጡት የአራዳ ከፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ መቅደስ ተስፋዬ የፌዴራል ኪራይ ቤቶች የመንግስት ቤቶች እንዲሁም በግል ይዞታ ላይ ለነበሩ ሰዎች ኤክስትራ ማይል ጭምር በመሄድ ለማስተካካል እየሞከርን ነው ብለዋል፡፡
ለምሳሌ በቀበሌ ቤት ላይ ለነበሩት ሁለት አማራጮች ነው የሰጠነው አንደኛው ኮንዶሚንየም ላይ ለመኖር ፍላጎት ያላቸው እና አቅም የሚፈቅድላቸውን ለይተናል በመንግስት ኪራይ ቤቶች ለመኖር ፍቃደኛ የሆኑትን በዕጣ አቅም በፈቀዱ ሁሉ ከክፍለ ከተማው እንዳይርቁ አድርገናል ብለዋል፡፡
የተሰጡት ቤቶችም መሰረተ ልማት የተሟላላቸው መሆናቸውንም ስራ አስፈፃሚዋ አስረድተዋል፡፡
የተማሪዎችንም ጉዳይ በተመለከተ ሰኞ ከአካባቢው ተነስቶ የሄደ ተማሪ በአካባቢው ትምህርት ቤት ማክሰኞ አንዲጀምር የስም ዝርዝር ጭምር እያስተላለፍን ነው ብለዋል፡፡
የሀገር ፍቅር ትያትር ቤት ይፈርሳል ወይ? ተብለው የተጠየቁት ስራ አስፈጻሚዋ አንደማይፈርስ አስረድተው በአካባቢውን በሚመጥን ደረጃ ግን እድሳት ይደረግለታል ብለዋል፡፡
ያሬድ እንዳሻው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Telegram: https://tinyurl.com/yc6tfzsw
Website: https://www.shegerfm.com/
Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Comments