ባለፉት 5 ወራት የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን እና የኦሮሚያ ክልል መንግስትን ሲያነታርክ የነበረዉ የባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ ፓርክ ጉዳይ መፍትሄ ማግኘቱ ተነግሯል፡፡
መጠለያዉ ከወራቶች በፊት ለኢንቨስተሮች ተሰጥቶ የነበረ ሲሆን ባለስልጣኑና የክልሉ መንግስት ባለሀብቶቹ ከያዙት መሬት ይልቀቁ አይለቁም በሚለዉ ጉዳይ ሲወዛገቡ ነበር፡፡
በዚህም ምክንያት አልሚዎቹ የተረከቡትን መሬት በማረሳቸዉ የደን ውድመት አድርሰዋል የተባለ ሲሆን 5 ሰዎች እና 5 ዝሆኖችም በዚሁ ጊዜ ሞተዋል፡፡
ታዲያ ሁለቱ አካላት በጉዳዩ ላይ አደረጉት በተባለዉ ውይይት፤ ባለሀብቶቹ ይዘዉት የነበረዉን ስፍራ ለቀዉ እንዲወጡ ተወስኗል ተብሏል፡፡
‘’አሁን ላይ ይህ ችግር ተፈቷል’’ ያሉት የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን የብሔራዊ ፓርኮች አስተዳደር መሪ ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር አዳነ ፀጋዬ ‘’ባለሀብቶቹ ከስፍራዉ እንዲወጡና ቦታዉ ለቀድሞ አገልግሎቱ እንዲመለስ መንግስት ውሳኔ አሳልፏል’’ ብለዋል፡፡
ባለሀብቶቹ ለ5 ወራት ይዘዉት የነበረዉን ስፍራ በመታረሱ የወደመዉ ደን ወደ ነበረበት እንዲመለስ የማድረግ ስራም ይሰራል መባሉንም ሰምተናል፡፡
ከዚህም ባለፈ በመጠለያ ውስጥ አሁንም ከሶማሌ እና ኦሮሚያ ክልሎች ወደ መጠለያዉ ገብተዉ የሰፈሩ ሰዎች አሉ ብለዋል ስራ አስፈፃሚዉ፡፡
‘’ይህ ካልተስተካከለ ፓርኩ ከአደጋ ነፃ ነዉ ማለት አይቻልም’’ ያሉ ሲሆን ሰዎቹን ከስፍራዉ ለማስወጣት ባለስልጣኑ ከክልልና ከፌደራል አካላት ጋር እየሰራበት ነዉ’’ ብለዋል፡፡
በባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ ፓርክ ዙሪያ ተሰጠ ስለተባለዉ መፍትሄ እና ዞኑ ሰጥቷል ስለተባለዉ የኢንቨስትመን ጉዳይ ወደ ኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሀረርጌ ዞን አስተዳዳሪ እና የዞኑ የአካባቢ ጥበቃ ኃላፊ ጋር ደዉለን የነበረ ቢሆንም ስልካቸዉ ባለመነሳቱ ምላሻቸዉ ማካተት አልቻልንም፡፡
ሸገር በዚህ ጉዳይ የሰራቸው የቀደሙ ዘገባዎች…
በረከት አካሉ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Telegram: https://tinyurl.com/yc6tfzsw
Website: https://www.shegerfm.com/
Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
コメント