top of page

መጋቢት 1 2017 - የባህር ማዶ ወሬዎች


ማርክ ካርኔይ አዲሱ የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊሆኑ ነው፡፡


ካርኔይ የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚሆኑት ተሰናባቹን ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶውን በመተካት የሌብራል የፖለቲካ ማህበሩ መሪ ሆነው በመመረጣቸው እንደሆነ ቢቢሲ ፅፏል፡፡


ማርክ ካርኔይ አዲሱ የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚሆኑት አገራቸው በአሜሪካ የታሪፍ ጫና ውስጥ በወደቀችበት አጋጣሚ ነው ተብሏል፡፡


በዚያ ላይ የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ካናዳን የአሜሪካ 51ኛዋ ግዛት አደርጋታለሁ ብለው ተነስተዋል፡፡


መጪው የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር አሜሪካውያን ስህተት ከመስራት ሊቆጠቡ ይገባል ማለታቸው ተሰምቷል፡፡


በንግድ ጦርነቱ አሜሪካን እናሸንፋታለን ብለዋል ካርኔይ፡፡


ማርክ ካርኔይ የሌብራል የፖለቲካ ማህበሩ መሪ ሆነው የተመረጡት 86 በመቶ ያህሉን ድምፅ በማግኘት እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡


ካርኔይ በመጪዎቹ ቀናት ቃለ መሐላ በመፈፀም የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚሆኑ ታውቋል፡፡



የሶሪያው ጊዜያዊ ፕሬዘዳንት አህመድ አል ሻራ በአገሪቱ ሰላም እንዲወርድ ተማፀኑ፡፡


መሰንበቻውን በአዲሱ የሶሪያ አስተዳደር የፀጥታ ሀይሎች እና በቀድሞው ፕሬዘዳንት ባሻር አል አሳድ ደጋፊዎች መካከል ተደጋጋሚ እና ከባድ ግጭት እየተፈጠረ መሆኑን አልጀዚራ ፅፏል፡፡


ከ740 በላይ የአልዋይት ማህበረሰብ ሰዎች መገደላቸው ታውቋል፡፡


ከመንግስት የፀጥታ ሀይሎች መካከል 125 ተገድለዋል ተብሏል፡፡


በአማፅያን ግፊት የቀድሞው ፕሬዘዳንት ባሻር አል አሳድ ከጥቂት ወራት በፊት ከአገር ከሸሹ ወዲህ የአሁኑ ግጭት በጣም ከባዱ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡


በግጭቱ 125 የቀድሞ ፕሬዘዳንት ደጋፊ ታጣቂዎች መገደላቸው ተሰምቷል፡፡


የተባበሩት መንግስታት ግጭቱ እንዲቆም እና የሰዎች እልቂት እንዲቆም ጥሪ ማቅረቡ ተሰምቷል፡፡



የኮንጎ ኪንሻሣ መንግስት በምስራቃዊ የአገሪቱ ክፍል የአማጺያኑን ጥምረት መሪዎች ይዞ ለማሰር ለሚረዱኝ የ5 ሚሊዮን ዶላር ወረታ እከፍላለሁ አለ፡፡


አማጺያኑ የኮንጎ ወንዝ ህብረት በሚባል ጥምረት መሰባሰባቸው ይነገራል፡፡


M 23 የተሰኘው አማጺ ቡድን የዚሁ ጥምረት አካል እንደሆነ ቢቢሲ ፅፏል፡፡


ላስያዛቸው ወረታ እከፍላለሁ ከተባለባቸው የአማጺያኑ የበላዮች መካከል የጥምረቱ መሪ ኮርኔል ናንጋ ዋነኛው መሆናቸው ታውቋል፡፡


የM 23 መሪዎች ሱልጣኒ ማኬንጋ እና በርትራንድ ቢሲምዋም በጥብቅ ይፈለጋሉ የተባሉ ናቸው፡፡


አማጺያኑ በቅርቡ የጎማ እና የቡካቩ ከተሞችን ጨምሮ በምስራቃዊ የአገሪቱ ክፍል ሰፊ አካባቢን በእጃቸው አስገብተዋል፡፡


የምስራቃዊ ኮንጎ ኪንሻሣው የፀጥታ መደፍረስ አለም አቀፋዊ አጀንዳ እስከመሆን ደርሷል፡፡

 

የኔነህ ከበደ

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page