top of page

መስከረም 9 2018 - ግንባታው ሲጀመር ከተያዘለት ወጪ ተጨማሪ 90 ሚሊዮን ዶላር የጠየቀው የሞጆ ደረቅ ወደብ ማስፋፊያ ፕሮጀክት፤ በቅርቡ ይመረቃል

  • sheger1021fm
  • Sep 19
  • 1 min read

ዘርፈ ብዙ አገልግሎት ይሰጣል የተባለው የሞጆ ደረቅ ወደብ ማስፋፊያ ፕሮጀክት በሁለት ወራት ውስጥ እንደሚመረቅ የተናገረው የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር ነው፡፡


የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ድኤታ ደንጌ ቦሩ ፕሮጀክቱ ከ240 ሚሊዮን ዶላር (በአሁኑ የምንዛሪ ተመን 38 ቢሊዮን ብር) በላይ ወጪ እንደተደረገበትና በሁለት ወራት ውስጥም እንደሚመረቅ ጠቅሰዋል፡፡


ከ6 ዓመት በፊት የሞጆ ደረቅ ወደብ ማስፋፊያ ፕሮጀክት በተጀመረበት ወቅት፤ የግንባታው ወጪ በ150 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር እንደነበረ መነገሩ ይታወሳል፡፡


በ2011 ዓ.ም ተጀምሮ ይጠናቀቃል ተብሎ ከተያዘለት ጊዜ 3 ዓመታትን የተሻገረው ፕሮጀክቱ ሲጀመር ከተያዘለት ወጪ ተጨማሪ 90 ሚሊዮን ዶላር መጠየቁ ተሰምቷል፡፡

ree

የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ድኤታ ደንጌ ቦሩ ኢትዮጵያ እያከናወነቻቸው ካሉ ትላልቅ ፕሮጀክቶች የሞጆ ደረቅ ወደብ ማስፋፊያ አንደኛው እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡


ሀገር ማደግ የምትችለው የሎጀስቲክስ ስርዓቷ ቀልጣፋ ሲሆን ነው ያሉት ሀላፊው፤ የሎጀስቲክስ ስርዓት ቀልጣፋ ካልሆነ የምንፈልገው እድገት ማምጣት አንችልም ብለዋል፡፡


ሚኒስትር ድኤታው ይህንን የተናገሩት፤ ስለ ሀገሪቱ የትራንስፖርት ዘርፉ እድገትና አሁን ያለበት ደረጃ፤ ከሰሞኑ በተለያዩ ዘርፍ ላሉ ባለሞያዎች ማብራሪያ በሰጡበት መድረክ ላይ ነው፡፡


ፕሮጀክቱ ይጠናቀቃል ተብሎ ከተያዘለት ጊዜ መዘግየቱ ከወራት በፊት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጭምር ጥያቄ ተነስቶበት፤ የሲሚንቶ እጥረት ግንባታው እንዲጓተት ካደረጉት ምክንያቶች ቀዳሚ መሆኑንም ተነግሮ ነበረ፡፡


ማንያዘዋል ጌታሁን


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…




Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page