መስከረም 9 2018 - የሸገር ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጋዜጠኞች፣ አርታኢ ትዕግስት ዘሪሁን እና ሪፖርተር ምንታምር ፀጋው፣ በፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቁጥጥር ስር ከዋሉ 17 ቀን ሆናቸው
- sheger1021fm
- Sep 19, 2025
- 1 min read
የሸገር ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጋዜጠኞች፣ አርታኢ ትዕግስት ዘሪሁን እና ሪፖርተር ምንታምር ፀጋው፣ በፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቁጥጥር ስር ከዋሉ 17 ቀን ሆናቸው፡፡
የፌዴራል ፖሊስ፣ ጋዜጠኞቹን በቁጥጥር ስር ያዋላቸው፣ ያሰራጩት ዘገባ በሕግ የተከለከለ ይዘት ያለውና የሽብር ድርጊት ነው ብሎ እንደሆነ፣ ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የጊዜ ቀጠሮ እንዲፈቅድለት፣ ባቀረበው ማመልከቻ ጠቁሟል፡፡
የሕክምና ባለሞያዎች፣ ለመንግስት ያቀረቡትን ጥያቄ ተከትሎ፣ የጤና ሚኒስቴር በሰርኩላር ያስተላለፈውን መፍትሄ፣ እንዴት እንደሚመለከቱት፣ የሕክምና ባለሞያ ቃለ መጠይቅ በማድረግ፣ ነሐሴ 24 በሸገር ኤፍ ኤም ሬዲዮ፣ ዜናው ተላልፎ ነበር፡፡
በዚሁ ዜና ምክንያት የፌዴራል ፖሊስ፣ ጋዜጠኞች ትዕግስት ዘሪሁን እና ምንታምር ፀጋውን፣ በቁጥጥር ስር ካዋለ በኋላ፣ ምክንያቱን ዘርዝሮ፣ የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠው በመጠየቁ፣ ፍርድ ቤቱ ዘጠኝ ቀን ፈቅዶለት ነበር፡፡

በቀጣዩ ቀጠሮ፣ የፌዴራል ፖሊስ የፎረንሲክ፣ የገንዘብ ዝውውራቸውን እና ተጨማሪ ምርመራዎችን ለማድረግ ተጨማሪ ቀናት ጠይቋል፡፡
የፌዴራል ፖሊስን ምክንያትና ከጋዜጠኞቹ የቀረበውን መከራከሪያ ያዳመጠው፣ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ጊዜ ቀጠሮ ወንጀል ችሎት ፣ ጋዜጠኞቹ በ50,000 ብር ዋስትና እንዲለቀቁ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
በትዕዛዙ መሰረት፣ መስከረም 7/2018 ከሰዓት በኋላ፣ አስፈላጊው ፎርማሊቲ ተሟልቶ፣ ለፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ደርሶታል፡፡
ይሁንና፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የከፍተኛ ፍ/ቤቱን ውሳኔ በይግባኝ፣ ወደ ፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመወሰዱ፣ ለመስከረም 12/2018 ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡
ጋዜጠኞቹም በእስር ላይ ናቸው፡፡
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s












Comments