መስከረም 9 2018 - ኢትዮጵያ የኒውክለር ቴክኖሎጂን ለሰላማዊ ዓላማ ለመጠቀም የጀመረችውን እንቅስቃሴ የዓለም አቀፉ የአቶሚክ ሀይል ተቆጣጣሪ ኤጀንስ ይደግፈዋል ተባለ
- sheger1021fm
- Sep 19
- 1 min read
የዓለም አቀፉ አቶሚክ ሀይል ተቆጣጣሪ ኤጀንስ ዋና ዳይሬክተር ራፋኤል ማርያኖ ግሮሲ ይህንኑ ማረጋገጣቸው ተነግሯል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ በለጠ ሞላ(ዶ/ር) ከዓለም አቀፉ አቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንስ ዋና ዳይሬክተር ጋር መወያየታቸው ተሰምቷል።
በኦስትሪያ ቪየና እየተካሄደ ባለው 69ኛው የየዓለም አቀፉ የአቶሚክ ሀይል ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ IAEA መደበኛ ጉባኤ ጎን ለጎን ውይይቱ መደረጉን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የማህበራዊ ትስስር ገፅ ተመልክተናል።

ውይይቱ ኢትዮጵያ በምታካሂደው የሰላማዊ ኒውክሌር ሃይል ፕሮግራም፣ በሰው ሃይል አቅም ግንባታ እና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ የዓለም አቀፉ አቶሚክ ሀይል ኤጀንስ በሚያደርጋቸው ድጋፎች ዙርያ ያተኮረ ነው ተብሏል።
ኢትዮጵያ የሰላማዊ ኒዉክሌር ኢነርጂ ፕሮግራሞችን እውን ለማድረግ መሠረት በመጣል ላይ መሆኗን እና ወደትግበራ ለመግባትም ሰፊ ጥረት እያደረገች መሆኗን ሚኒስትሩ አብራርተዋል ተብሏል።
በዚህ ኢትዮጵያ በምትጀምረው ብሄራዊ የኒውክለር ሃይል ግንባታ ላይ የቴክኒክ ድጋፍ እና የእውቀት ሽግግር ማድረግ ወሳኝ በመሆኑ ኤጀንስው በዚህ ረገድ ድጋፍ እንዲያደርግ መጠየቃቸው ተነግሯል።
በተለይም በግብርናው እና በጤናው ዘርፍ በኢትዮጵያ የተጀመሩ ስራዎች ከኤጀንሲው ከፍተኛ ድጋፍ ይፈልጋሉ ብለዋል።
የዓለም አቀፉ አቶሚክ ሀይል ተቆጣጣሪ ኤጀንስ ዋና ዳይሬክተር ራፋኤል ማርያኖ ግሮሲ በውይይቱ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ጋር በቅርቡ በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸውን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ የኒውክለር ቴክኖሎጂን ለሰላማዊ መንገድ ለመጠቀም የጀመረችውን እንቅስቃሴም የዓለም አቀፉ አቶሚክ ሀይል ተቆጣጣሪ ኤጀንስ እንደሚደግፍም ማረጋገጫ መስጠታቸው ተሰምቷል።
ቴዎድሮስ ወርቁ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s












Comments