መስከረም 9፣2017 - ኢትዮ ቴሌኮም በዘንድሮ በጀት ዓመት በቴሌኮምና በዲጅታል አገልግሎት የተሻለ አቅም ለመፍጠር ለመሰረተ ልማት ግንባታ ከ1 ቢሊዮን በላይ ዶላር በጀት መመደቡን ተናገረ
- sheger1021fm
- Sep 19, 2024
- 2 min read
ኢትዮ ቴሌኮም በዘንድሮ በጀት ዓመት በቴሌኮምና በዲጅታል አገልግሎት የተሻለ አቅም ለመፍጠር ለመሰረተ ልማት ግንባታ አንድ ቢሊዮን በላይ ዶላር በጀት መመደቡን ተናገረ።
አምና 93.7 ቢሊየን ብር ገቢ ያገኘው ኢትዮ ቴሌኮም በዘንድሮ በጀት አመት 163.7 ቢሊየን ብር ገቢ ለማግኘት ማቀዱን አስረድቷል።
ይህም ከአምናው ሲነፃፀር የ70 ቢሊየን ብር ብልጫ እንዳለው ታውቋል።
አሁን 78 ሚሊየን ደንበኞች ያሉት ኩባንያው በእቅዱ መሰረት የደንበኞቹን ቁጥር ወደ 83 ሚሊዮን ለማድረስ አቅጃለሁ ብሏል።
የቴሌብር ደንበኞችም ከ47.5 ሚሊየን ወደ 55 ሚሊየን ከፍ ለማድረግ ማቀዱን ተናግሯል።
ኢትዮ ቴሌኮም በሀገር ከተደረገው የፋይናንስና የገንዘብ ስርዓት ለውጥ ጋር በተጣጣመ መልኩ የ2017 እቅድ መንደፋንም ሰምተናል።
ኩባንያው ከመንግስት ፖሊሲ እና ከተለያዩ የቢዝነስ ስራና ጠባይ ጋር የሚስማማ እቅድ ቀርፆ ወደ ስራ መግባቱን አስረድቷል።
በዚህ የአንድ ዓመት የስራ ዘመን እቅድና የ3 ዓመት ጉዞ እቅድ አለም አቀፍ የቴሌኮም ባህሪና የሀገር ውስጥ የማክሮ ኢኮኖሚውን ማሻሻያ ያካተተ መሆኑን የኩባንያው ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ ዛሬ ለጋዜጠኞች ነግረዋል።

በቴሌኮምና በዲጅታል ፋይናንስ የውደድር ገበያው የተረጋጋ እንደሚሆን ኩባንያው በእቅዱ ታሳቢ አድርጓል።
ዛሬ ላይ ኢትዮ ቴሌኮም ከቴሌኮምና ከዲጂታል መሰረተ ልማት ጋር በተገናኘ ጥሩ አቋም ላይ መድረሱን አስረድቷል።
በግል፣ በማህበራዊ እንዲሁም በመንግስት አገልግሎት ማእዘን በአጠቃላይ በሀገር ምርት እድገት(GDP) ላይ ብዙ የዲጂታል አገልግሎት በቀጥታ እንደሚያቀርብ ማቀዱን ሰምተናል።
በጅምር ያሉ ቢዝነሶች እንዲያድጉ፣ አዳዲስ የዲጅታል ስራም ወደ ገበያው እንዲገባና አጠቃላይ የኢንተርኔት ኢኮኖሚ ጉልበት እንዲኖር ለማድረግ እንደሚሰራ ኩባንያው አረጋግጧል።
የዲጅታል ዘርፍ የማይነካካው ነገር ስለሌለ እቅዱ በኢንተርኔት አማካኝነት የሚደረገው ማስፋፍያ ተከትሎ ቀጥተኛ የኢኮኖሚ እድገት እንዲኖር ታሳቢ ያደረገ ነው ተብሏል።
በ2017 ኩባንያው አዳደኢስ የቴሌኮምም የዲጅታልም መሰረተ ልማት ለመገንባትና ለማስፋፋት ማቀዱን ተናግሯል።
በእቅዱ መሰረትም 1298 አዲስ የሞባይል ጣቢያ በአንድ ዓመት እገነባለሁ ብሏል።
በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ ከዚህ ቀደም የ4ጂ ያላገኙ 500 ከተሞች እንዲሁም 15 ከተሞች ደግሞ የ 5ጂ አገልግሎት እንዲያገኙ ማቀዱን ኩባንያው ተናግሯል።
ከቢዝነስ አዋጭነት ማእዘን ውጭ በአጠቃላይ 496 የገጠር ከተማን ኮኔክት ለማድረግ በጀት ማዘጋጀቱን በእቅዱ አካቷል።
በ 2017 የስራ ዘመን በኢንተርኔት በድምፅና በሌላም መሰረተ ልማት መአዘን ከፍተኛ አቅም እገነባለሁ ብሏል።
ኩባንያው በኢትዮዽያ ቀዳሚ የዲጅታል መፍትሄ አቅራቢ ኩባንያ በመሆኑ የክላውድ የዳታ ሴንተርና በሌሎችም ግዙፍ መሰረተ ልማት ላይ ማስፋፍያው በብርቱ እንደሚገነባ አስረድቷል።
ተህቦ ንጉሴ
Comments