ቶታል ኢነርጂስ በአውሮፓ ሀገሮች ደረጃ ነው የተሰራው ያለውን የነዳጅ ማደያ በአዲስ አበባ አስመረቀ፡፡
በዛሬው ዕለት የተመረቀው የቶታል ኢነርጂስ የነዳጅ ማደያ ላለፉት 45 ዓመታት አገልግሎት ሲሰጥ የነበረና በ73 ሚሊየን ብር የመልሶ ግንባታ የተደረገለት መሆኑ ተነግሯል፡፡
ማደያው በከፍተኛ የጥራት ደረጃ የተሰራ እና በአንድ ጊዜም 10 ተሽከርካሪዎችን ነዳጅ ማጠጣት የሚችል መሆኑ ተነግሮለታል፡፡
በተደረገለት ማሻሻያም ነዳጅ የመያዝ አቅሙ ከ80 ወደ 200 ሜትር ኪዩብ እንዳደገም ሰምተናል፡፡
መኪና ማጠቢያ፣ ጥገና ቦታ፣ የገበያ ማዕከላት የተሟሉለት መሆኑ የተነገረ ሲሆን በቅርቡ ደግሞ ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ሀይል መሙያ እንደሚገነባለት ተነግሯል፡፡
በአዲስ መልክ የተገነባው የቦሌ መንገድ የቶታል ኢነርጂስ ነዳጅ ማደያን ያነፁት ኢትዮጵያዊያን መሆናቸው ተሰምቷል፡፡
በምርቃት ስነ ስርዓቱ ላይ የቶታል ኢነርጂስ ብራንድ አምባሳደር አትሌት ሀይሌ ገብረስላሴ፣ የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ፣ በኢትዮጰያ የፈረንሳይ አምባሳደርን ጨምሮ ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
ከሁለት ዓመት በፊት ከቶታል ወደ ቶታል ኢነርጂስ ስሙን የቀየረው ኩባንያው በኢትዮጵያ ከ70 ዓመት በላይ ሰርቷል፡፡
ንጋቱ ሙሉ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… https://bit.ly/33KMCqz
Commentaires