መስከረም 8፣2017 - የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ የት ደረሰ?ወደ ትግበራስ መች ይገባ ይሆን?
- sheger1021fm
- Sep 18, 2024
- 1 min read
ኢትዮጵያ መጋቢት ወር ላይ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ያጸደቀችው የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ የት ደረሰ?
ወደ ትግበራስ መች ይገባ ይሆን?
የፍትህ ሚኒስቴር አማካሪ ታደሰ ካሣ(ዶ/ር) በዚህ ዓመት ትግበራው ይጀመራል ብለዋል፡፡
የሽግግር ፍትህ ልዩ ዐቃቤ ህግ ልዩ ችሎት የእውነት ምህረት እና ማካካሻ ኮሚሽን እንዲሁም የሁሉም ተቋማት ማቋቋምያ አዋጆች ረቂቅ ተዘጋጅቷል ብለዋል፡፡
ጥቅምት ወር ላይ ሁሉም ረቂቆች እንዲያልቁ በወሩ መጨረሻ ደግሞ በሁሉም ረቂቆች ላይ የህዝብ ውይይት እንዲካሄድ እና ግብረ መልስ እንዲሰበሰብ ታቅዷል ብለዋል ታደሰ ካሣዶ/ር፡፡
በህዳር ወር ደግሞ የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ከሚሰራቸው የመጀመሪያ ስራዎቹ ዋናው የሽግግር ፍትህ ተቋማትን ማቋቋምያ አዋጆችን ማጽደቅ እንዲሆን ነው አቅደን እየሰራን ያለነው ብለዋል፡፡
አሁን ኢትዮጵያ ያለችበት የሰላም ሁኔታ ለሀገራዊ ምክክር እንቅፋት መሆኑን እየተነረ ነው የሽግግር ፍትህ ለመተግበር ምቹ ሁኔታ አለ ውይ? ላልናቸው ጥያቄ፤ ታደሰ ካሣ(ዶ/ር) ‘’ለኔ የሽግግር ፍትህን ለመተግበር ከዚህ የተሻለ ገዜ አለ ብዬ አላስብም’’ ሲሉ መልሰዋል፡፡
‘’በአንዳንድ አካባቢዎች ያለው ግጭት እንቅፋት ሊሆን ይችላል የሽግግር ፍትህ የሚፈልገው አንዱ እና መሰረታዊው ጉዳይ ሰላም ነው’’ ብለዋል አማካሪው፡፡
ህዝብ እንደ ልቡ የሚንቀሳቀስበት የፖለቲካ አውድ ከሌለ የሽግግር ፍትህን እውን ለማድረግ እንደሚያዳግት ጠቁመዋል፡፡
‘’አሁን ያለው የሰላም ሁኔታ የራሱ ስጋት አለው ግን ተስፋ ያደረግነው ፈጠነም ዘገየም የትግራይ ክልል ግጭት በተፈታበት መንገድ የኦሮሚያም የአማራም ክልል ችግር ይፈታል ብለን እናስባለን’’ ብለዋል፡፡
የሽግግር ፍትህን ለመተግበር የሚቋቋመው ኮሚሽን እና የሚመረጡ ኮሚሽነሮች ልክ እንደ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን እና ኮሚሽነሮች ቅሬታ እንዳይነሳባቸው ምን ታስቧል? የተባሉት ታደሰ ካሣ(ዶ/ር) ‘’በህዝብ የሚታመኑ የህዝብ ተቀባይነት ያላቸው ኮሚሽነሮች እንዲመረጡ ይደረጋል’’ የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
በኮሚሽነሮች መረጣ ላይ የመንግስት ጣልቃ ገብነት እንዳይኖርም ይሰራል ብለዋል፡፡
ሙሉ ዘገባውን በድምፅ ለማድመጥ
ያሬድ እንዳሻው
Comments