መስከረም 8፣2017 - ''አገልግሎት ፍለጋ ከሀገር ውጭ ከሚወጣው ምንዛሪ 50 ሚሊዮን ዶላር አድኛለሁ'' የኢትዮጵያ ጠለፋ መድን
- sheger1021fm
- Sep 18, 2024
- 1 min read
የኢትዮጵያ ጠለፋ መድን(Ethiopian Reinsurance) አገልግሎት ፍለጋ ከሀገር ውጭ ከሚወጣው ምንዛሪ 50 ሚሊዮን ዶላር አድኛለሁ አለ፡፡
ግለሰቦች እና ደርጅቶች በህይወት፣ በንብረት እና በሌሎች በሚደርሱባቸው አደጋዎች ሽፋን የሚሰጡ የኢንሹራን ኩባንያዎችን ሽፋን ለመስጠት የተቋቋመው የኢትዮጵያ ጠለፋ መድን በስራ ላይ 8 ዓመታት ማስቆጠሩ የተነገረለት ሲሆን በ1 ቢሊዮን ብር የተቋቋመ ድርጅት መሆኑ ተነግሮለታል፡፡
ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የመድን አገልግሎት ፍለጋ በተለያዩ ሀገራት በተቋቋሙ ኢንሹራንስ ሰጭ ድርጅቶች ዘንድ ይሄዱ እንደነበር የተናገሩት የኢትዮጵያ ጠለፋ መድን ሥራ አስፈፃሚ አቶ ፍቅሩ ፀጋዬ አገልግሎቱንም የሚያገኙት በውጭ ምንዛሪ ነበር ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ጠለፋ መድን ( #Ethiopian_Reinsurance ) ከተቋቋመ በኋላ ግን 50 ሚሊየን ዶላር ማትረፍ ችለናል፤ የተለያዩ ተቋማትም ወደ ድርጅታችን በመምጣት አገልግሎቱን ማግኘት ጀምረዋል ብለዋል አቶ ፍቅሩ፡፡

ከስምንት አመታት በፊት የReinsurance አገልግሎት ፍለጋ 30 በመቶው ገንዘብ ከሀገር ይወጣ እንደነበር የተናገሩ ሲሆን በሌላ በክልል ደግሞ ከ10 የአፍሪካ አገራት ጋር በጋራ በመስራት የውጭ ምንዛሬ እያስገኘን ነው ይላሉ፡፡
67 በመቶ ገደማው በኢንሹራንስ ኩባንያዎች ባለቤቶቹ የተያዘው የኢትዮጵያ ጠለፋ መድን ወይም Ethiopian Reinsurance 31 ከመቶው ደግሞ በሰባት ባንኮች የተቋቋመ መሆኑን ሰምተናል፡፡
ከመንግስት እና ከግል የተውጣቱ ባለሃብቶች ያቋቋሙት ይሄው ማህበር 40 በመቶው የባለቤትነት ድርሻው የመንግስት ነው ያሉት አቶ ፍቅሩ ቀሪው 60 በመቶው ደግሞ የግል ዘርፉ ነው ብለዋል፡፡
ለስምንት ዓመታት ከከወንኳቸው ተግባራት በበለጠ ለመስራት በሶስት ምዕራፍ ከፋፍዬ ለአስር ዓመት የምተገብረው ዕቅድ መያዜንም እወቁልኝ ብሏል፡፡
በአለማቀፍ ደረጃ ከ300 በላይ የReinsurance ድርጅቶች አሉ የተባለ ሲሆን በአፍሪካ ደግሞ 52 እንደሆኑ ተነግሯል፡፡
ኢትዮጵያም አፍሪካ ውስጥ ካሉ የReinsurance ድርጅቶች የ29ኛ ደረጃን ይዛለች ያሉት አቶ ፍቅሩ ከዚህ በላይ ደረጃዋን ለማሻሻል ደግሞ ድርጅቱ ለመጭው 10 ዓመታት የሚከውናቸው ስራዎች ትልቅ ሚና አላቸው ተብሏል፡፡
ሙሉ ዘገባውን በድምፅ ለማድመጥ
ፋሲካ ሙሉወርቅ
Comments