top of page

መስከረም 6፣2017 - ኢሰመኮ በኢትዮጵያ ከህግ አግባብ ውጭ የሚደረግ የሰዎች እስር፣ አፈናና አስገድዶ መሰወር መኖሩን በክትትል ሪፖርቱ ማረጋገጡን በተደጋጋሚ ይናገራል

  • sheger1021fm
  • Sep 16, 2024
  • 2 min read

መንግስታዊው የኢትየጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን(ኢሰመኮ) በኢትዮጵያ ከህግ አግባብ ውጭ የሚደረግ የሰዎች እስር፣ አፈናና አስገድዶ መሰወር መኖሩን በክትትል ሪፖርቱ ማረጋገጡን በተደጋጋሚ ይናገራል፡፡


ኮሚሽኑ በተጠናቀቀው ዓመት 2016 ዓ.ም በፖሊስ ጣቢያዎች አደረግኩት ባለው ክትትል በተለይም “በወቅታዊ ሁኔታ” በሚል የሚያዙ ተጠርጣሪዎችን በ48 ሰዓት ውስጥ ወይም በጭራሽ ፍርድ ቤት አለማቅረብ፣ በፍርድ ቤት ነፃ የተባሉ፣ የዋስትና መብታቸው የተጠበቀላቸው እንዲሁም የምርመራ መዝገባቸው በዐቃቤ ሕግ አያስከስስም ተብሎ የተዘጋ ሰዎችን አስሮ ማቆየት፣ በወንጀል ተጠርጣሪዎች ምትክ የቤተሰብ አባላትን ማሰር፣ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች በአስተዳደር አካላት፣ በመከላከያ ሰራዊት እና በፖሊስ አባላት ጭምር ሰዎችን ከሕግ ውጭ ማሰር እንዳለ ማረጋገጡን በክትትል ሪፖርቱ አካትቷል፡፡


በአብዛኛው እንዲህ ዓይነቱ እስር ፖለቲካዊ መልክ ያለው ነው ያሉን የደብረ ታቦር ዩንቨርሲቲ የህግ መምህርና ጠበቃው አቶ መሳፍንት አላቸው ናቸው፡፡


በህዝቡ ዘንድ በ #ፖለቲካ ተሳትፏቸው ተለይተው የሚታወቁ፤የማታወቁም ቢሆኑ መንግስት የፖለቲካ ተቀናቃኝ ናቸው የሚላቸው ግለሰቦች እየታደኑ በምሽት ሳይቀር እየታፈኑ ሲወሰዱ መመልከት የተለመደ ሆኗል ይላሉ፡፡


ታዋቂ የሆኑት አንዳንድ ጊዜ ይፈቱ የሚል ዘመቻ ይከፈትላቸዋል፤ የማይታወቁት ደግሞ ለዓመታት እስር ቤት ይማቅቃሉ፤ የት እንደታሰሩ ሳይታወቅ፣ክስም ሳይመሰረትባቸው ታስረው ለዓመታት ቆይተው በድንገት በነፃ ይለቀቃሉ ይላሉ፡፡


በዚህ መንገድ የሚደረገው እስር የግለሰቦችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማዳከም ሆን ተብሎ በፖለቲከኞች ትዕዛዝ የሚደረግ ህገወጥ ተግባር መሆኑን በስራቸው ምክንያት እንዳስተዋሉ የህግ መምህርና ጠበቃው አቶ መሳፍንት ነግረውናል፡፡


የኢትዮጵያ #የወንጀለኛ_መቅጫ_ህግም ይሁን በህገመንግስቱ እንደተቀመጠው በህግ ቁጥጥር ስር የሚውሉ ሰዎች ወንጀሉን እጅ ከፍንጅ እስካልፈፀመ መብቱ ተጠብቆ መያዝ እንዳለበት ተቀምጧል የሚሉት አቶ መሳፍንት የህግ አካላት በወንጀል ተጠረጠሩ ሰዎችን የሚያዙበት መንገድ አንዳንድ ጊዜ አግባብነት እንደሚጎድለው ያነሳሉ፡፡


በህጉ የተቀመጠውንና በወንጀል ተጠረጠሩ ሰዎች መያዝ ያለባቸው ከጠዋት 12 ሰዓት እስከ ምሽት 12 ሰዓት ድረስ፣ በምን ወንጀል እንደተጠረጠሩ ተነግሯቸው፣ ከፍርድ ቤት የወጣ የትዕዛዝ ወረቀት በመያዝ እንደሆነም ባለሙያው ጠቅሰዋል፡፡


እንዲህ ዓይነቱ ክስ ፖለቲከኞች እጃቸውን ስለሚያስገቡበት ተጨባጭ ያልሆኑ ክሶችና ውንጀላዎች የሚበዙበት ነው፣ ፖለቲከኞች የህግ ጉዳይን ለህግ ሰዎች ሰጥተው ከዚህ ሊወጡ ይገባል፣በአንድ ወቅት አሳሪ የነበረው ሌላ ጊዜ ደግሞ ታሳሪ ሲሆን ተመልክተናል፣የህግ የበላይነት ወደ ቦታው መመለስ አለበት ሲሉም ምክረ ሃሳባቸውን ሰጥተውናል፡፡



ምንታምር ፀጋው

Commentaires


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page