top of page

መስከረም 6፣2017 - መስከረም 6፣2017 - የባህር ማዶ ወሬዎች


የሱዳን መንግስት ጦር በሰሜናዊ ዳርፉር በፈፀመው የአየር ድብደባ ስድስት የገዛ ራሱን እግረኛ ወታደሮችን ገደለ ተባለ፡፡


ጦሩ ነገሩ እጄን በእጄ የሆነበት በኤል ፋሸር ከተማ እንደሆነ ሱዳን ትሪቢዩን ፅፏል፡፡


የአየር ድብደባው የተፈፀመው የአርኤስ(RSF) ታጣቂዎች ወደ ከተማዋ ሰርገው ለመግባት ሙከራ ባደረጉበት ወቅት ነው ተብሏል፡፡


የሱዳን መንግስት ጦር እና የRSF ታጣቂዎች በከተማዋ ውጊያ ከገጠሙ ቆይተዋል፡፡


አጠቃላይ ጦርነቱ ከአመት ከ5 ወራት በላይ ሆኖታል፡፡


ጦርነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሰብአዊ ቀውሱን እያከፋው ነው ይባላል፡፡


በአየር ድብደባው ከተጠቀሰውም በላይ ሰዎች ሳይገደሉ እንዳልቀረ በዘገባው ተጠቅሷል፡፡


በእስያዊቱ ሀገር ማያንማር የደረሰ ከባድ ጎርፍ ከ100 በላይ ሰዎችን ገደለ፡፡


በጎርፍ ሕይወታቸው ካለፈው ሌላ 64 ሰዎች ደግሞ የገቡበት እንዳልታወቀ ቢቢሲ ፅፏል፡፡


በአገሪቱ ከባድ ጎርፍ የደረሰው በዚያ ያጋጠመውን ከባድ አውሎ ነፋስ ተከትሎ ነው ተብሏል፡፡


በከባዱ ጎርፍ ምክንያት ከ320,000 በላይ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በየመጠለያው ለማረፍ መገደዳቸው ተሰምቷል፡፡


ማያንማር የገጠማት የአውሎ ነፋስ አደጋ ከምንግዜው የከፋ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡


ጎርፍ እና አውሎ ነፋሱ ከ66 ሺህ በላይ ቤቶችን ማፈራረሱ ታውቋል፡፡


የአገሪቱ መንግስት አጣዳፊ አለም አቀፍ እርዳታ እንዲደረግለት ጥሪ አቅርቧል ተብሏል፡፡



የእስራኤለ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ የየመን ሁቲዎች ወደ እስራኤል የባልስቲክ ሚሳየል ለተኮሱበት ድርጊት የእጃቸውን እንሰጣቸዋለን አሉ፡፡


ኔታንያሁ ሁቲዎቹ ከባድ ዋጋ ይከፍላሉ ማለታቸውን ቢቢሲ ፅፏል፡፡


በሁቲዎቹ የተተኮሰው ሚሳየል እስከ እስራኤል ማዕከላዊ ክፍል መድረሱ ታውቋል፡፡


በሚሳየል መከላከያ ጋሻ የተመታው ባልስቲክ ሚሳየል ስብርባሪ በአንድ የባቡር ጣቢያ ላይ የተወሰነ ቁሳዊ ጉዳት አደርሷል ተብሏል፡፡


ባለፈው ሐምሌ ወር ሁቲዎቹ ወደ ቴል አቪቭ በሰደዱት ሰው አልባ አጥቂ በራሪ አካል /ድሮን/ አንድ ሰው ተገድሏል፡፡


እስራኤል በምላሹ የየመኑን ሁዴይዳ ወደብ እና አካባቢውን በመምታት መጠነ ሰፊ ጉዳት ማድረሷን መረጃው አስታውሷል፡፡



ሪፖብሊካውያን የፖለቲካ ማህበር ወክለው በአሜሪካ ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ የሚፎካከሩት ዶናልድ ትራምፕ የግድያ ሙከራ ሊቃጣባቸው ነበር ተባለ፡፡


በትራምፕ ላይ የግድያ ሙከራው ሊቃጣባቸው የነበረው በፍሎሪዳ የጎልፍ መጫወቻ ስፍራቸው እንደነበር የደህንነት ሹሞች መናገራቸውን ቢቢሲ ፅፏል፡፡


ጥቃት አድራሹ AK - 47 የተሰኘውን ዓይነት አውቶማቲክ ጠመንጃ ታጥቆ ከጎልፍ መጫወቻው በ500 ሜትር ገደማ በሚርቅ ጫካ ውስጥ አድፍጦ ነበር ተብሏል፡፡


መታየቱን እንዳወቀም በፍጥነት መኪናውን አነስቶ ለመሸሽ ሙከራ ማድረጉ ታውቋል፡፡


ተጠርጣሪው ተይዞ መታሰሩ ተሰምቷል፡፡


ትራምፕ ወዲያው ደህንነታቸው ወደሚጠበቅበት ስፍራ ተወስደዋል ተብሏል፡፡


የቀድሞው ፕሬዘዳንት ከዚህ አጋጣሚ በኋላ ከምርጫው በጭራሽ ምንም ነገር እንደማያግዳቸው ተናግረዋል፡፡


ከ2 ወራት በፊትም በፔንሴልቫኒያ በምርጫ ቅስቀሳ ላይ እያሉ ተተኩሶባቸው የቀኝ ጆሯቸው ክፍል በጥይት ተመትቶ መትረፋቸውን መረጃው አስታውሷል፡፡


የኔነህ ከበደ

コメント


bottom of page