በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ትግራይ ክልል ውስጥ የወደሙ ትምህርት ቤቶች አሁንም ድረስ እየተጠገኑ አይደለም ተባለ፡፡
የፌዴራል መንግስት የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለመገንባት የሚያደርገው ጥረት እጅግ ዝቅተኛ ነው ተብሏል፡፡
በጦርነቱ ምክንያት ትግራይ ውስጥ የነበሩ 2492 ትምህርት ቤቶች ወድመዋል፣ በክልሉ ከነበሩ 46,598 መምህራን ውስጥ 14 ሺ የሚሆኑት በሞት፣ በአካል ጉዳትና መሰል ችግሮች ምክንያት በመምህርነት አልቀጠሉም፡፡
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ኪሮስ ጉዕሽ(ዶ/ር) በትግራይ ክልል ውስጥ የትምህርት መሰረተ ልማቶች በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ወድመዋል፡፡
መሰረተ ልማቶቹን ጠግኖ ወደ ስራ ለማስገባት ጥናት ቢደረግም ዛሬም ድረስ ከፌዴራል መንግስትና ከሌሎች ረጂ ተቋማት በቂ ድጋፍ እየተደረገ አይደለም ያሉ ሲሆን ይህም ትምህርት ዘርፉን እየጎዳው ነው ብለዋል፡፡
በ2016 የትምህርት ዘመን ትግራይ ክልል ውስጥ 2.4 ሚሊየን ተማሪዎች ለመመዝገብ ታቅዶ የተሳካው ግን 1 ነጥብ 2 ሚልየን ብቻ መሆኑን ሰምተናል፡፡
ከዚህ በላይ ተማሪዎቹ 3 ዓመት መማር የነበረባቸው እድሜ ስላለፋቸው ይህን ማካካሱ ደግሞ ሌላ ስራ ነበር የሚሉት ዶክተር ኪሮስ አሁንም ድረስ ሙሉ ለሙሉ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ሥርዓቱ ማስገባት አልተቻለም ይላሉ፡፡
ዛሬም ድረስ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች የተፋናቃይ እና ስደተኛ መጠለያ ናቸው ፣ ሌሎች ትምህርት ቤቶች ደግሞ በጊዜያዊ አስተዳደሩ ስር እየተዳደሩ አይደሉም ተብሏል፡፡
ይህም በመሆኑለ 6 ዓመታት የአካባቢው ልጆች ወደ ትምህርት ገበታቸው መመለስ አልቻሉም ሲሉ የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊው ዶክተር ኪሮስ አስረድተዋል፡፡
ክልሉ በዚህ ሁሉ ችግር ውስጥም ሆኞ ተማሪዎችን እያስተማረ ነው ይላል፡፡ በ2016 የ12ተኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ወስደው ጥሩ ውጤት ተመዝግቧል ሲሉ ነግረውናል፡፡
ትግራይ ክልል ውስጥ ያሉ ህፃናት ወደ ትምህርት ቤት እንዲመለሱ ቅድሚያ መሰረተ ልማቶች መሟላት አለበት የተባለ ሲሆን ለዚህም ሲባል የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ የመገንባቱ ስራ ችላ ሊባል አይገባል ሲሉ ዶክተር ኪሮስ አሳስበዋል፡፡
ሙሉ ዘገባውን በድምፅ ለማድመጥ ይህንን ይጫኑ...
በረከት አካሉ
Comments