top of page

መስከረም 30 2018 - በፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ስር ያሉ ታራሚ ተማሪዎች በ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና የማሳለፍ ምጣኔ ከሀገራዊ የማሳለፍ ምጣኔ ከእጥፍ በላይ መሆኑ ተነገረ፡፡

  • sheger1021fm
  • Oct 10
  • 2 min read

በፌደራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ስር በአባ ሳሙኤል ማረሚያ ማዕከል የሚገኘው የታራሚዎች ትምህርት ቤት፤ በ2017 የትምህርት ዘመን ያስፈተናቸው ተማሪዎች በቀጥታ እና በረመዲያል መቶ በመቶ ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባቸውን ነጥብ እንዳስመዘገቡም ሰምተናል፡፡


በፌደራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ስር ሆነው የ2017 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ፈተና ከተፈተኑት አጠቃላይ ተማሪዎች መካከል 85 በመቶ የሚሆኑት በቀጥታ እና በረመዲያል ወደ #ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባቸውን ነጥብ አስመዝግበዋል ተብሏል፡፡


በሀገር አቀፍ ደረጃ የ2017 ትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ፈተና ከወሰዱት መካከል 50 ከመቶና ከዚያ በላይ ያመጡት 8.9 በመቶ ሲሆኑ በፌዴራል ማረሚያ ውስጥ የሚገኙ ት/ቤቶች ካስፈተኗቸው ተማሪዎች መካከል ደግሞ 26.4 በመቶ የሚሆኑት ከ50 በመቶ በላይ አምጥተዋል።


በፌደራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ስር በአባ ሳሙኤል ማረሚያ ማዕከል ፈተናው ከወሰዱ 24 ተማሪዎች 12ቱ በመደበኛው 12ቱ ደግሞ በረመዲያል ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባቸውን ነጥብ ማስመዝገባቸውን ሰምተናል፡፡


በፌደራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ስር አምስት ትምህርት ቤቶች ያሉ ሲሆን፤ እነዚህም በቃሊቲ፣ በዝዋይ፣ በሸዋሮቢት፣ በድሬዳዋ እና በአባ ሳሙኤል ማረሚያ ማዕከል የሚገኙ ናቸው፡፡


ከእነዚህም ዉስጥ በተለምዶ አባሳሙኤል ተብሎ በሚጠራው ማረሚያ ማዕከል ትምህርት ቤት 24 ተማሪዎች እንዲሁም በዝዋይ ማረሚያ ቤት ያለው ትምህርት ቤት ደግሞ 44 ተማሪዎችን የ2017 ዓ.ም 12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና አስፈትነው ነበረ ተብሏል፡፡


የአባሳሙኤል ማዕከል ካስፈተናቸው ተማሪዎች በቀጥታ እና በረመዲያል መርሀ ግብር ሁሉም ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባቸውን ነጥብ አስመዝግበዋል ተብሏል፡፡


በዝዋይ ከተፈቱኑት 44 #ታራሚ ተማሪዎች መካከል 6ቱ በቀጥታ 28ቱ ደግሞ በረመዲያል እንዳለፉ ሰምተናል፡፡


ይህንን የነገሩን በፌደራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን የትምህርትና ስልጠና መሪ ስራ አስፈፃሚ አስመራ አብደታ ናቸው፡፡

ree

በፌደራል ማረሚያ ማዕከላት የሚገኙ ት/ቤቶች የ12ኛ ክፍል ፈተናን ለ3 ተከታታይ ዓመታት እንዳስፈተኑ የሚጠቅሱት ሀላፊው በሶስቱም ዓመታት ከሀገራዊ የማሳለፍ ምጣኔ በላይ ማሳለፋቸውንም አስታውሰዋል፡፡


በአሁኑ ወቅት በፌደራል ማረሚያ ማዕከላት የሚገኙ 5 ት/ቤቶች ውስጥ 1,300 ተማሪዎች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡


ለመሆኑ በማረሚያ ተቋማት ውስጥ ትምህርት ተከታትለው የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተናን ያለፉ ታራሚዎች የቀጣይ እጣ ፈንታ ምንድነው ስንል አቶ አስመራን ጠይቀናቸዋል፡፡


ለዚህም 4 አማራጮች እንደተለዩ ነገረውናል፡፡ የመጀመሪያው የይቅርታ መስፈርት የሚያሟሉትን ከፍትህ ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር በይቅርታ መመዘኛ መፈታት የሚችሉት በይቅርታ መፍታት ነው ብለውናል፡፡


ሁለተኛው ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር ማረሚያ ቤቶች ውስጥ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ካምፓስ ከፍተው ተማሪዎቹ ትምህርታቸው እንዲከታተሉ ማድረግ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡


ሶስተኛው አማራጭ በማረሚያ ተቋማት ውስጥ እስከ ደረጃ 5 የቴክኒክና ሞያ ትምህርት ቤቶች ስላሉ በእነዚያ ማካተት እና ማስተማር መሆኑንም አስረድተዋል፡፡


በስፖንሰርም ሆነ ከፍለው መማር የሚችሉት ታራሚ ተማሪዎች ባሉበት በሆነው፤ የርቀት ትምህርት በሚሰጡ የግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አማካኝነት መማር እንደ አራተኛ አማራጭ የተያዘው እንደሆነ ከአቶ አስመራ ሰምተናል፡፡


በይቅርታ የሚታለፉት ከታለፉ፤ ከባባድ ውንጀሎች ፈፅመው በህግ ጥላ ስር ያሉት በእንዴት አይነት ይስተናገዳሉ፤ ከህግ እንጻርስ እንዴት ይታያል ያልናቸው ስራ አስፈፃሚው፤ ታራሚዎቹ የመማር መብት እንዳላቸው አስታውሰው እነዚህ ግን እዚያው ባሉበት ሆነው እንዲማሩ በሚያስችሉት አማራጮች ነው የሚስተናገዱት ብለውናል፡፡


ትምህርት ሚኒስቴር በዚህ ረገድ አዎንታዊ ምላሽ እንዲሰጠን እንጠበቃለን ያሉት ሀላፊው፤ በተለይ ዩኒቨርሲቲዎች በማረሚያ ቤቶች ገብተው ትምህርት እንዲያስተምሩ እንደሚችሉ ተሞክሮም አለ ይላሉ፡፡


በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ስር አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ፤ በአርባ ምንጭ ማረሚያ ቤት ውስጥ የራሱ ካምፓስ ከፍቶ 12ኛ ክፍልን የጨረሱ ተማሪዎች እያስተማረ እንደሆነ ሰምተናል፡፡ አቶ አስመራም ይህንን በፌደራል ማረሚያ ቤቶችም መተግበር ይቻላል የሚል እምነት አላቸው፡፡


እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ነገር ግን በተስፋ መቁረጥ እና በሌሎች ምክንያቶች የመማር ፍላጎት አጥተው በማረሚያ ተቋማት የሚገኙ ታዳጊዎችን ትምህርት እንዲጀምሩ እየተሰራ ነው ተብሏል፡፡


ከፌደራል ማረሚያ ቤት ስር ካሉት 5ቱ ማዕከላት በተጨማሪ ክልሎች ስር በሚገኙ ማረሚያ ቤቶች ውስጥ ባሉ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ታራሚዎች እንዳሉም ተነግሯል፡፡


ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ….


ማንያዘዋል ጌታሁን ያዘጋጀውን በምህርት ስዩም

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page