top of page

መስከረም 30፣2017 - የባህር ማዶ ወሬዎች


የሩሲያ መንግስት ዩክሬይን የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት(NATO) አባል የመሆን ፍላጎቷን እርግፍ አድርጋ ካልተወች በስተቀር ከኪየቭ ጋር አንዳችም ሰላም አይኖረንም አለ፡፡


ዩክሬይን የኔቶ አባል የመሆን ፍላጎቷ የቆየ እንደሆነ አረብ ኒውስ አስታውሷል፡፡


ይሄ የኪየቭ አቋም በሩሲያ በኩል በፍጹም ተቀባይነት የለውም ያሉት የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይዋ ማሪያ ዛኻሮቫ ናቸው፡፡


ሩሲያ የዩክሬይን ልዩ ዘመቻዋን ከከፈተችባቸው ምክንያቶች መካከል የኔቶን ወደ ዩክሬይን የመስፋፋት ውጥን መግታት አንዱ እንደሆነ ዛሐሮቫ ተናግረዋል፡፡


የዩክሬይኑ ጦርነት ከ2 ዓመት ከመንፈቅ በላይ ሆኖታል፡፡


በወቅታዊው የመካከለኛው ምስራቅ የጦር ውጥረት የተነሳ ብዙ አየር መንገዶች የአፍጋኒስታንን የአየር ክልል ምርጫው እያደረጉ ነው ተባለ፡፡


ኢራን ባለፈው ሳምንት ወደ እስራኤል 180 ሚሳየሎችን መተኮሷን ተከትሎ በሁለቱ አገሮች መካከል ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚለው ስጋት አይሏል፡፡


በዚህም የተነሳ ቀደም ብሎ በኢራን የአየር ክልል በኩል ያልፉ የነበሩ አየር መንገዶች መስመሩን እየተውት ነው ተብሏል፡፡


ለኢራን የአየር ክልል አማራጭም በአፍጋኒስታን በኩል እያለፉ መሆኑን ሚድል ኢስት ሞኒተር ፅፏል፡፡


የአፍጋኒስታንን የአየር ክልል የሚገለገሉ አውሮፕላኖች ብዛት በጣሙን እየጨመረ መምጣቱ ተጠቅሷል፡፡


ቀደም ሲል የአውሮፓ ህብረት የአቪየሽን ደህንነት ተከታታይ መስሪያ ቤት የአባል አገሮች አየር መንገዶች አውሮፕላኖች የኢራንን የአየር ክልል እንዳይጠቀሙ መምከሩን መረጃው አስታውሷል፡፡



የእስራኤሉ የመከላከያ ሚኒስትር ዮአብ ጋላንት በኢራን ላይ የምንወስደው የአፀፋ ወታደራዊ እርምጃ የአገሪቱ መሪዎች ከሚጠብቁትም ሆነ ከሚገምቱት በላይ የከፋ ይሆናል አሉ፡፡


እስራኤል ከሳምንት በፊት በኢራን 180 ሚሳየሎች እንደተተኮሱባት አናዶሉ አስታውሷል፡፡


የእስራኤል ሹሞች ኢራን ለዚህ ድርጊቷ የእጇን ታገኛለች ሲሉ ሰምብተዋል፡፡


የመከላከያ ሚኒስትሩ ዮአብ ጋላንት በኢራን ላይ የምንወስደው እርምጃ ዒላማውን የጠበቀ እና ደምሳሽ ከመሆኑም በላይ የኢራን መሪዎች ሊረዱት ከሚችሉት በላይ ይሆንባቸዋል ማለታቸው ተሰምቷል፡፡


የኢራን ሹሞች በእስራኤል ላይ የሚሳየል ጥቃት ካስፈፀሙ በኋላ እስራኤል አፀፋውን እመልሳለሁ ካለች ይበልጥ እቶን እሳት እናዘንብባታለን ሲሉ ዝተዋል፡፡


በሌላ መረጃ የእስራኤሉ የመከላከያ ሚኒስትር በአሜሪካ ሊያደርጉት የነበረው ጉብኝት መሰረዙ ተሰምቷል፡፡


በቀዳሚው ቀጠሮ መሰረት ቢሆን ኖሮ ጋላንት ከትናንት በስቲያ ወደ ዋሽንግተን ያመሩ ነበር፡፡


የመከላከያ ሚኒስትሩ የአሜሪካ ጉብኝት መሰረዝ እስራኤል በኢራን ላይ ለመውሰድ ካቀደችው ወታደራዊ እርምጃ ጋር ተያይዞ እየተነሳ ነው፡፡


የኔነህ ከበደ


Comments


bottom of page