ኢትዮጵያ ከ3 ዓመት በኋላ (እ.አ.አ በ2027) የሚደረገው ዓለም አቀፍ የሎጂስቲክስ ጉባኤ ለማስተናገድ መመረጧን ተነገረ።
የኢትዮጵያ የዕቃ አስተላላፊዎችና የመርከብ ወኪሎች ማህበር በሰጠው መግለጫ ይህን አለም አቀፍ ጉባኤ ለማዘጋጀት 4 ጊዜ ውድድሮች ማድረጓንና ሳይሳካ መቅረቱን ተናግሯል።
ለዚህም እንደምክንያት የሆነው በኢትዮጵያ ያለው ጦርነትና የሰላም እጦት፣ ተፎካካሪ ሀገራት የተሻለ የውድድር ሃሳብ ይዘው ይገኙ ስለነበር መሆኑን በመግለጫው ተነስቷል።
ዓለም አቀፉ የዕቃ አስተላላፊዎች ማህበር ፌዴሬሽን እንደ ጎርጎሮሲያኑ የዘመን አቆጣጠር ከ1926 ጀምሮ ይህንን ጉባኤ ሲያካሄድ ነበር ያለው ማህበሩ በዚህ ጉባኤ በተለያዩ የሎጀስቲክስ ኢንዱስትሪው ዐቢይ ጉዳዮች ላይ ይመክርበታል ተብሏል።
ኢትዮጵያ ይህንን ጉባኤ ስታስተናግድ ኢትዮጵያዊያን ባለሞያዎች ከአለም አቀፍ የዘርፉ ባለሞያዎች ጋር እንዲገናኙ እድል ይከፍታል የተባለ ሲሆን ሀገሪቱ የአፍሪካ የሎጀስቲክስ አገልግሎት ማዕከል ለማድረግ በሚደረገው እንቅስቃሴ ጥሩ እድል ይሰጣል ሲል ማህበሩ አስረድቷል።
በጉባኤው ሁሉም አባል ሀገራት እንደመገኘታቸው ግዙፍ አለም አቀፍ የሎጀስቲክስ ድርጅቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉድርጅቶች ጋር አብረው እንዲሰሩም እድል ይሰጣል ተብሏል።
ዓለማ አቀፉ የዕቃ አስተላላፊዎች ማህበር ፌዴሬሽን 113 የሎጂስቲክስ ብሔራዊ ማህበራት አባል የሆኑበት ሲሆን 40 ሺህ የሚሆኑ በዓለም ዙሪያ ያሉ የዕቃ አስተላላፊ ድርጅቶች እና የሎጂስቲክስ ኩባንያዎች የተወከሉበት ነው።
ዓለም አቀፍ የሎጂስቲክስ ጉባኤ በአፍሪካ ከዚህ በፊት ደቡብ አፍሪካ እና ግብፅ ያስተናገዱ ሲሆን ኢትዮጵያ 3ተኛ ሀገር እንደ አፍሪካ ትሆናለች።
ይህ ጉባኤ የኢትዮጵያ የዕቃ አስተላላፊዎችና የመርከብ ወኪሎች ማህበር ተወዳድሮ ያሸነፈ ቢሆንም ጉባኤው ኢትዮጵያ የምትወከልበት በመሆኑ ከመንግስት ጋር አብሮ እየሰራ መሆኑን ማህበሩ አስረድቷል።
በጉባኤው ከ1,500 እስከ 2,000 ሰዎች ይታደሙበታል ተብሎ ይጠበቃል።
በረከት አካሉ
Comentarios