top of page

መስከረም 29፣2016 - የባህር ማዶ ወሬዎች



የእስራኤል ጦር የፍልስጤማውያን ይዞታ በሆነው የጋዛ ሰርፅ የአየር እና የሚሳየል ድብደባውን ማክፋቱ ተሰማ፡፡


የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ በጋዛ ሐማስ እና ተቀጥላዎቹን ለመደምሰስ ታላቅ ሀይል እንጠቀማለን ማለታቸውን ቢቢሲ ፅፏል፡፡


ገና ምን ታየና ማለታቸው ተሰምቷል ኔታንያሁ፡፡


ሐማስ እስራኤል ላይ በፈፀመው ጥቃት የተገደሉት እስራኤላውያን ብዛት 900 ያህል መድረሱ ተሰምቷል፡፡


በሐማስ ድንገት ደራሽ ጥቃት ከተገደሉት መካከል 260ዎቹ በአንድ የሙዚቃ ድግስ ላይ የነበሩ ሰዎች ናቸው ተብሏል፡፡


እስራኤል ጋዛ ውስጥ በፈፀመችው የአፀፋ ጥቃት ደግሞ 700 ያህል ፍልስጤማውያን እንደተገደሉ ተጠቅሷል፡፡


ብዙ ሰዎችም በሐማስ ታግተው ወደ ጋዛ ሰርፅ መወሰዳቸው ታውቋል፡፡


እስራኤል ከአፀፋ ጥቃቷ በተጨማሪ ወደ ጋዛ የነዳጅ ዘይት እንዳይደርስ አድርጋለች ምግብ እንዳያልፍ ከልክላለች፡፡


ኤሌክትሪክ እና ውሃም ማቋረጧ ተሰምቷል፡፡



#በሌላ_በኩል ትውልደ እስራኤል #ፈረንሳዊያን የእስራኤልን ጦር ለመቀላቀል ወደ ቴል አቪቭ እየጎረፉ ነው ተባለ፡፡


ብዙዎቹም ትውልደ እስራኤል ፈረንሳዊያን የእስራኤል ጦር ተጠባባቂዎች እንደሆኑ አናዶሉ ፅፏል፡፡


የእስራኤል ጦር በመቶ ሺህዎች ለሚቆጠሩ ተጠባባቂዎች ጥሪ ማቅረቡን ዘገባው አስታውሷል፡፡


ትውልደ እስራኤል ፈረንሳውያን የተጠባባቂው ጦር አባላት ባገኙት አውሮፕላን ወደ እስራኤል እየመጡ ነው ተብሏል፡፡


ይህም ጦርነቱ ይበልጥ እየተካረረ መምጣቱን እንደሚያሳይ ተጠቅሷል፡፡


የፈረንሳይ መንግስት ትውልደ እስራኤል የአገሪቱ ተጠባባቂዎችን በመልቀቁ ከአንዳንድ ወገኖች ትችት እየቀረበበት መሆኑ ተሰምቷል፡፡



የአውሮፓ ህብረት ለፍልስጤማውያን የሚሰጠውን የልማት እርዳታ ሊያቋርጥ ነው፡፡


የህብረቱ ኮሚሽን ለፍልስጤማውያን የሚሰጠውን የልማት እርዳታ እንደሚያግድ እወቁልኝ ማለቱን አናዶሉ ፅፏል፡፡


ህብረቱ ለፍልስጤማውያ ሲሰጥ የቆየውን እርዳታ አቋርጣለሁ ያለው በእስራኤል እና በሐማስ መካከል ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ እንደሆነ ታውቋል፡፡


የአውሮፓ ኮሚሽን የፍልስጤማውያ የጦር እና የፖለቲካ ድርጅት ሐማስ በእስራኤል ላይ ቅዳሜ እለት የከፈተውን ጥቃት የሽብር ተግባር ሲል ጠርቶታል፡፡


ከህብረቱ በተጨማሪ ጀርመን እና ኦስትሪያም በየፊናቸው ለፍልስጤማውያ ሲሰጡ የቆዩትን የልማት እርዳታ ማቋረጣቸው ተሰምቷል፡፡



በካሜሮኗ ርዕሰ ከተማ ያውንዴ ባለፈው እሁድ በደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ የደረሱበት የጠፋውን ማፈላለጊያ የነፍስ አድን ጥረት መቀጠሉ ተሰማ፡፡

የአደጋው ሟቾች ብዛት 27 መድረሱ ታውቋል፡፡


የመሬት መንሸራተቱ ከገደላቸው በተጨማሪ ከ50 በላይ ሰዎች ደግሞ አካላዊ ጉዳት እንደገጠማቸው አፍሪካ ኒውስ ፅፏል፡፡


ጎርፍ እና የመሬት መንሸራተቱ አርቆ የወሰዳቸው ሰዎች እንዳሉ እማኞች ተናግረዋል፡፡


በከተማዋ ጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት አደጋ የደረሰው በዚያ ሲጥል የነበረውን ዶፍ ዝናብ ተከትሎ መሆኑ ታውቋል፡፡


አደጋው የአየር ለውጡ ውጤት ተደርጎ እየተቆጠሩ መሆኑን ዘገባው አስታውሷል፡፡



የኔነህ ከበደ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… https://bit.ly/33KMCqz

Comments


bottom of page