መስከረም 28፣2017 - የትግራይ የፀጥታ ሀይሎች ባወጣው መግለጫ በሚወጡት መግለጫዎች ህዝቡ መረበሹን ተናግሮ ይህንን እንደማይታገስ አስረድቷል
- sheger1021fm
- Oct 8, 2024
- 1 min read
የትግራይ የፀጥታ ሀይሎች ትናንት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ በጊዜአዊ አስተዳደሩ እና በደብረፂዮን ገ/ሚካኤል(ዶ/ር) በሚመራው ህወሃት በሚያወጡት መግለጫዎች ህዝቡ መረበሹን ተናግሮ ይህንን እንደማይታገስ አስረድቷል፡፡
በጊዜአዊ አስተዳደር አቶ ጌታቸው ረዳና በደብረጺዮን ገ/ሚካኤል(ዶ/ር) በሚመራው ህወሃት መካከል የተፈጠረው አለመግባባት በክልሉ ነዋሪ ላይ ስጋት መፍጠሩን ተደጋግሞ ተነግሯል፡፡
የነደብረፂዮን የህወሃት ቡድን ትናንት ባወጣው መግለጫ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዘዳንት ጌታቸው ረዳን ጨምሮ የተለያዩ ባለስልጣናት ማንሳቱን መናገሩ ይታወሳል፡፡
የራሴን አዲስ ካቢኔም አቋቁሚያለሁ ያለ ሲሆን አቶ ጌታቸውን ተክቶ በፕሬዚዳንትነት የሚያገለግለውን ሰው በተመለከተ ከፌዴራል መንግስት ጋር እንነጋገርበታለን ብሎ ነበር፡፡
ይህን ተከትሎ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ባወጣው መግለጫም መፈንቅለ መንግስት ታውጆብኛል በዝምታም አልመለከትም ብሏል፡፡

ጊዜአዊ አስተዳደሩ ይህን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ በደብረ ጺዮን ገ/ሚካኤል የሚመራው ቡድን መፈንቅለ መንግስት አውጆብኛል ሲል ከሷል፡፡
የጊዜአዊ አስተዳደሩ መግለጫም በዚህም ለሚፈጠረው ማንኛውም ዓይነት ጥፋት ብቸኛው ተጠያቂ የደብረጺዮን ቡድን መሆኑን አስረድቷል፡፡
ጊዜአዊ አስተዳደሩ ሥርዓት አልበኝነትን ሥርዓት ለማስያዝ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ ጠቁሟል፡፡
በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው ጊዜአዊ አስተዳደር የደብረጺዮን ቡድን ባወጣው መግለጫም መፈንቅለ መንግስት አውጆብኛል ሲል ከሶ ይህንንም በትዕግስት እንደማይመለከትና ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ ተናግሯል፡፡
ታዲያ ይህ የሁለቱ የመግለጫ ምልልስ በሕዝብ ውስጥ መረበሽ ፈጥሯል ያለው የትግራይ የፀጥታ ሀይሎች ባወጣው አጭር መግለጫ ችግር ሲፈጠር ዝም ብለን አንመለከትም ብሏል፡፡
የፀጥታ ሀይሎች መግለጫ የትግራይን ሰላምና ደንነትን እንደሚያረጋግጥ ጠቁሞ ሥርዓት አልበኝነት እንዲፈጠር አንፈቅድም፣ ሲፈጠርም በዝምታም አንመለከትም ሲል ተናገሯል፡፡
የፀጥታ ሀይሎች መግለጫ የትኛውንም ቡድን ሥርዓት እንደሚያሲዝ በስም አልጠቀሰም፡፡
በደብረጺዮን ቡድን የሚመራው ሕወሓት በማዕከላዊ ቁጥጥር ኮሚሽኑ በኩል በሰጠው መግለጫ ከሕወሃት አባልነት የተባረሩ በማንኛውም ቦታ እና ጊዜ በሕወሃት ስም ፖለቲካዊ ስራ እና እንቅስቃሴ ማድረግ አይችሉም ማለታቸው ይታወሳል፡፡
ያሬድ እንዳሻው
Comentarios