መስከረም 28፣2017 - አዋሽ ባንክ እና አዋሽ ኢንሹራንስ 30ኛ ዓመት የምሥረታ በዓላቸውን ማክበር ጀመሩ
- sheger1021fm
- Oct 9, 2024
- 2 min read
እህት ኩባንያዎቹ በተለያዩ መርሐ-ግብሮች የሚከበረውን የ30ኛ ዓመት የምስረታ በዓላቸውን ማብሰሪያ በዛሬው ዕለት በዋናው መ/ቤታቸው በይፋ አስጀምረዋል።
30ኛ ክብረ- በዓሉ በተከታታይ ለሶስት ወራት በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል ተብሏል፡፡
አዋሽ ባንክና አዋሽ ኢንሹራንስ በዘርፉ ላለፉት 30 ዓመታት ከወቅቱ ጋር እራሳቸውንና የአገልግሎት አሰጣጣቸውን እያዘመኑ በመሄድ ከፍተኛና ተከታታይነት ያለው ዕድገት አስመዝግበዋል፣ ዘርፉንም በቀዳሚነት በመምራት ላይ ይገኛሉ ሲሉ ስራ አስፈጻሚዎቹ ተናግረዋል፡፡
አዋሽ ባንክ የተመሰረተው የዛሬ 30 ዓመት እ.ኤ.አ. ህዳር 10 ቀን 1994 ዓ.ም በ486 መስራች ባለአክሲዮኖች 24.2 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ነው፡፡
ዛሬ 30ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በሚያከብርበት ወቅት የባንኩ ባለአክሲዮኖች ቁጥር ከ11ሺ በላይ የደረሰ ሲሆን የተከፈለው የካፒታል መጠን ደግሞ ከ20.3 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡
በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት ውስጥ ካፒታሉ ወደ ብር 55 ቢሊዮን ያድጋል ተብሎ ይጠበቃል ሲል ዋና ስራ አስፈጻሚው ጸሃይ ሽፈራው ተናግረዋል፡፡

የባንኩ አጠቃላይ ሀብት መጠን አሁን ላይ ከ282 ቢሊዮን ብር በላይ፣ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑ ደግሞ ከ255 ቢሊዮን በላይ ብር ደርሷል ተብሏል፡፡
የሰጠው ብድር መጠን በአሁኑ ወቅት ብር 194 ቢለዮን ደርሷል፣ ከ954 በላይ ቅርንጫፎችን አሉት ሲብል ሰምተናል፡፡
አዋሽ ባንክ ባለፉት 30 ዓመታት ከ33 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ትርፍ በማግኘት ለመንግስት ከ7 ቢሊዮን ብር በላይ የትርፍ ገቢ ግብር ከፍሏል ተብሏል፡፡
ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ በመቶ ሚሊዮኖች በሚቆጠር ገንዘብ ወጪ በማድረግ ማህበራዊ ሀላፊነቱን ተወጥቷል ሲሉ ስራ አስፈጻሚው አስረድተዋል።
አዋሽ ባንክ በአዲስ አበባ ባለ 18 ወለል እና ባለ 16 ወለል ያላቸውን መንትያ ህንጻዎችን ከእህት ኩባንያው ከአዋሽ ኢንሹራንስ አ.ማ ጋር በመሆን የራሱ ዋና መስሪያ ቤት ህንጻ አለው፡፡
የባንኩን እጅግ ዘመናዊና በርዝመቱም ለሀገራች ትልቁ የሆነውን የዋና መ/ቤት ሕንጻ ለመገንባት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 10,551 ካሬ ሜትር ቦታ መረከቡ ይታወሳል፡፡

በተመሳሳይ እ.ኤ.አ. ጥቅምት 1 ቀን 1994 ዓ.ም በ456 መስራች ባለአክሲዮኖች በብር 4.9 ሚሊዮን በተክፈለ ካፒታል የተመሠረተው አዋሽ ኢንሹራንስ አ.ማ. 30 ዓመቱን ማክበር ጀምሯል፡፡
በመጀመሪያ የሥራ ዓመቱ 15 ሚሊዮን ብር ጠቅላላ የተፃፈ አረቦን ለመሰብሰብ የቻለው አዋሽ ኢንሹራንስ አሁን ላይ 3.12 ቢሊዮን ብር በላይ ጥቅል የተፃፈ አረቦን በመሰብሰብ ከሌሎች የግል የመድን ድርጅቶች የበላይነት ስፍራውን ይዞ ይገኛል ሲባል ሰምተናል።
የተከፈለ ካፒታሉ 1.9 ቢሊዮን ብር ፣የተመዘገበ ካፒታሉ ደግሞ 4 ቢሊዮን ብር ሆኖ የባለአክሲዮኖቹን ቁጥር ወደ 2,016 አድገዋል ሲሉ ዋና ስራ አስፈጻሚው ጅባት ፋጂ ተናግረዋል፡፡
የኩባንያው አጠቃላይ ሀብት ከብር 7.7 ቢሊዮን በላይ የደረሰ መድረሱን ዋና ስራ አስፈጻሚው አስረድተዋል፡፡
30ኛ ዓመት የምስረታ በዓላቸውን ማክበር የጀመሩት አዋሽ ባንክና አዋሽ ኢንሹራንስ ክብረ በዓላቸው ለተከታታይ ለሶስት ወራት በተለያዩ ዝግጅቶች ይቆያል ተብሏል፡፡
Commentaires