top of page

መስከረም 27፣2016 - ኢትዮጵያዊው ቢሊየነር መሀመድ አል አሙዲ በስዊድን ሀገር ያላቸውንና የነዳጅ ኩባንያቸውን ሊሸጡት ማሰባቸው ተሰማ


ኢትዮጵያዊው ቢሊየነር መሀመድ አል አሙዲ በስዊድን አገር ያላቸውንና ፕሪም ተብሎ የሚጠራውን የነዳጅ ኩባንያቸውን ሊሸጡት ማሰባቸው ተሰማ።


በኮራል ፔትሮሊየም ሆልዲንግስ ስር የሚተዳደረው ፕሪም ሆልዲንግስ ኤቢ የነዳጅ ኩባንያ በስዊድን ሀገር ትልቁ የኢነርጂ ኩባንያ ሲሆን በስካንዲኔቪያ ሀገሮች የላቀ ታዳሽ ሀይል አቅራቢ  መሆኑም ተነግሯል።

የኩባንያው የወደፊት ሂደቱ እንዲወሰን ስትራቴጂያዊ አማራጮችን እንዲፈለጉ

ባለቤቱ ትውልደ ኢትዮጵያዊው  አል-አሙዲ  ለኮራል የዳይሬክተሮች ቦርድ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸው ተሰምቷል።


ውሳኔውም የኩባንያውን አብዛኛ ወይንም ሙሉ በሙሉ የአክሲዮን ድርሻ ሽያጭ ሊያጠቃልል እንደሚችል ተጠቅሷል።


ቦርዱ የኩባንያውን ባለድርሻዎች ታሳቢ ያደረገ፣ በአጠቃላይ የቡድኑን የፋይናንስ አቋም ለማጠናከር ያለመ እንዲሁም በባለቤቱ በአላሙዲ ቤተሰብ ውስጥ ለተተኪ የመልቀቅ ፍላጎትን ከግምት ያስገባ ውሳኔ እንዲሰጥ ይጠበቃል ተብሏል።


ሂደቱም ፕሪም በስዊድን ውስጥ ወሳኝ መሠረተ ልማት የዘረጋ  እንደሆነ ከግምት ውስጥ ማስገባት እንዳለበት ተዘግቧል።


ኩባንያው በስዊድን ከ550 በላይ የነዳጅ ማደያዎች  እንዳሉት የተነገረ ሲሆን በጎተንበርግ እና ላይሴኪል ውስጥ ሁለት የነዳጅ ማጣሪያዎች አሉት ተብሏል።


ይህም ከስዊድን 80 በመቶው ፣ከኖረዲክ ሀገሮችን 40 በመቶ ነዳጅ የማጣራት አቅም እንደሆነ ተጠቅሷል።


ፕሪም በዓመት እስከ 18 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ነዳጅ የማጣራት አቅም እንዳለው ተነግሯል።

ኩባንያው በአሁኑ ጊዜ በታሪኩ ከፍተኛውን ለውጥ በማካሄድ ይገኛል የተባለ ሲሆን እ.ኤ.አ. በ2035 ከባቢን የማይጎዳ ታዳሽ ሀይል እና እንደ ነጃጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ የመሳሰሉ ባህላዊ የሀይል ምንጮች የሚባሉትን በማምረት ትርፋማ ለመሆን አቅዶ እየሰራ መሆኑ ተነግሯል።


ባለፈው ዓመት ፕሪም ሆልዲንግስ የ161 ቢሊዮን የስዊድን ክሮነር ወይንም 14.6 ቢሊዮን ዶላር ሽያጭ እና 14.8 ቢሊዮን ክሮነር (1.3 ቢሊዮን ዶላር) ትርፍ ማስመዝገቡን ኩባንያው ባወጣው መግለጫ ተናግሯል።


ንጋቱ ሙሉ

Comments


bottom of page