top of page

መስከረም 25፣2016 - በካርቱም የኢትዮጵያ ኤምባሲ ላይ ጉዳት ያደረሰው የትኛው ተፋላሚ ወገን እንደሆነ አልታወቀም


በካርቱም በሚገኘውን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ላይ ጉዳት ያደረሰው የትኛው ተፋላሚ ወገን እንደሆነ እስካሁን አልታወቀም፡፡


ሁለቱም ተፋላሚ ሀይሎች ጉዳት ያደረሰውን፤ አንዱ በሌላው ላይ እየጠቆመ ነው፡፡


በካርቱም የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባለፈው ማክሰኞ ረፋድ ላይ በደረሰበት የከባድ መሳሪያ ጥቃት ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት መዘገቡ ይታወሳል፡፡


የከባድ መሳሪያው ምት የኤምባሲውን ሕንፃ እና ንብረት ክፉኛ ቢጎዳም በሰው ሕይወት ላይ ግን የደረሰ አደጋ እንደሌለ ቢቢሲ የኤምባሲውን ዲፕሎማት ዋቢ አድርጎ ዘግቧል፡፡


በኢትዮጵያ ኤምባሲ ላይ የደረሰውን ጉዳት በብርጋዴር ጄኔራል መሐመድ ሃምዳን ዳጋሎ የሚመራው የፈጥኖ ደራሽ ሀይል ያወገዘው በዚያው ዕለት ነበር፡፡


ፈጥኖ ደራሹ ሀይሉ በቲዊተር ገፁ፤ ተቀናቃኙን ጄኔራል አብዱልፋታህ አል ቡርሃንን ለድርጊቱ ተጠያቂ አድርጎ ‘’አረመኔያዊ ድርጊት’’ ሲል አውግዞታል፡፡


ጀኔራል አብዱራህማን የሚመሩት የሱዳን መከላከያ በበኩሉ፣ የፈጥኖ ደራሹን ሀይል መግለጫ አስተባብሎ “እኛ አላደረግነውም” ብሏል፡፡

“የታጣቂው ሀይል የእራሱን ወንጀል በኛ ላይ ለማላከክ የሰጠው አስተያየት የሚያሳፍር ነው” ሲልም ከጥቃቱ ጀርባ የፈጥኖ ደራሹ ሀይል እንዳለበት መናገሩን ዘ ኢስት አፍሪካን ዘግቧል፡፡


ስለዚህ ጉዳት ያደረሰው ሀይል ማንኛውም እንደሆነ ለጊዜው አልታወቀም፡፡


በኢትዮጵያ መንግስት በኩልም እስካሁን ይፋዊ መግለጫ አልተሰጠም፡፡


በካርቱም የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ግን ድርጊቱን በማውገዝ መግለጫ ማውጣቱንና በአለም አቀፍ ደረጃ ጥበቃ በሚደረግላቸው ተቋማት ላይ እንዲህ ዓይነት ድርጊት ዳግም እንዳይፈፀም መጠየቁን ካርቱም ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሰምተናል፡፡


የኢትዮጵያ ኤምባሲ በተመታበት ዕለት፤ የአረብ ኢሚሬስት፤ የሩሲያና የደቡብ አፍሪካ ኤምባሲዎች ጥቃት እንደደረሰባቸውና በርካታ ሀገሮች ኤምባሲያቸውን እየዘጉ፣ ዲፕሎማቶቻቸውን ከካርቱም እየወጡ ነው ተብሏል፡፡


በሱዳን 6 ወራት ባስቆጠረው ጦርነት ከ3,000 በላይ ሰዎች መገደላቸውና ከ6,000 በላይ በመቁሰላቸው እንዲሁም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩት መፈናቀላቸው እየተነገረ ነው፡፡



የኔነህ ሲሳይ


የሸገርንወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… https://bit.ly/33KMCqz

Comments


bottom of page