መስከረም 24፣2017 - ያንጎ ለተገልጋዮቼ እና ለአሽከርካሪዎቼ የዲጅታል ክፍያ ለማሻሻል እና የጤና አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ ስራዎችን እየከወንኩ ነው አለ
- sheger1021fm
- Oct 4, 2024
- 1 min read
የሜትር ታክሲ አገልግሎት የሚሰጠው ያንጎ ለተገልጋዮቼ እና ለአሽከርካሪዎቼ የዲጅታል ክፍያ ለማሻሻል እና የጤና አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ ስራዎችን እየከወንኩ ነው አለ፡፡
በዚህም ድርጅቱ ከአዋሽ ባንክ እና ከአማካሪ ዶክተሮች ጋር ውል ማሰሩን ተናግሯል፡፡
ስምምነቶቹ የተሳፋሪዎችን የጉዞ ልምድ ከማሳደግ በተጨማሪ ለያንጎ አጋር አሽከርካሪዎች ጤና እና ደህንነት ቅድሚያ የሚሰጡ ናቸው ተብሎላቸዋል፡፡
በአዋሽ ባንክ እና በሜትር ታክሲ አገልግሎት ላይ የተሰማራው ያንጎ መካከል የተደረገው ስምምነት የባንኩ ሰራተኞች እና ደንበኞች የያንጎ መተግበሪያን በመጠቀም ለሚያደርጉት የመጀመሪያዎቹ ሶስት ጉዞዎች የ15 በመቶ ቅናሽ ይደረግላቸዋል ብሏል፡፡
ይህ ስምምነት የዲጂታል መፍትሄዎችን ተደራሽነት በማስፋት እና ዝቅተኛው የህብረተሰብ ክፍል የዲጅታል ባንኪንግ አገልግሎቶችን እንዲጠቀም ይረዳል ያሉት በኢትዮጵያ የያንጎ ስራ አስኪያጅ ዶክተር የቀናዓለም አበበ ከአዋሽ ባንክ ጋር በመተባበር የክፍያ ሂደቱን ለማቅለል ይረዳል ብለዋል፡፡

ይህ ትብብር በኢትዮጵያ እያደገ በሚገኘው የትራንስፖርት ዘርፍ ላይ ዲጂታል ክፍያዎች ደረጃቸውን ጠብቀው ተደራሽ እንዲሆኑም ያስችላል መባሉን ሰምተናል፡፡
በሌላ በኩል ያንጎ የሜትር ታክሲ አገልግሎት ድርጅት በቴሌሜድስን እና በህክምና አገልግሎት ከሚሰጠው ከአማካሪ ዶክተሮች ጋር የመግባቢያ ስምምነት ፈርሟል፡፡
በስምምነቱ መሰረት አማካሪ ዶክተሮች በሁሉም የህክምና አገልግሎቶች ላይ ለያንጎ አጋር አሽከርካሪዎች ቅናሽ በመስጠት ተመጣጣኝ የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ ያደርጋል ተብሏል፡፡
በተጨማሪም የያንጎ አሽከርካሪዎች አማካሪ ዶክተሮች ለደንበኞቻቸው ከሚያቀርቡት የቴሌሜዲሲን ምክር አገልግሎት ላይ የመጀመሪያዎቹን 30 ደቂቃ ነፃ ተጠቃሚ ይሆናሉ የተባለ ሲሆን በዚህ መሰረት አሽከርካሪዎች ከቤታቸው ሆነው ወይም በጉዞ ላይ እያሉ ይህንን አገልግሎት ማግኘት ይችላሉ ብለዋል ስራ አስኪያጁ፡፡
ብዙ ጊዜ በመንገድ ላይ ረጅም ሰዓት ማሳለፍን በሚጠይቀው ስራ እና በዚህም ምክንያት መደበኛ የህክምና አገልግሎትን ለማግኘት ሰዓት አይኖራቸውም የሚሉት የአማካሪ ዶክተሮች ዋና ስራ አስፈፃሚ ቴዎድሮስ ወርቁ አሽከርካሪዎቹ ካሉበት ሆነው የህክምና ምክር እንዲያገኙ ስምምነቱ ያግዛል ብለዋል፡፡
ያንጎ ግሩፕ ዋና መስሪያ ቤቱን በዱባይ ያደረገ የቴክኖሎጅ ኩባንያ ነው፡፡
ፋሲካ ሙሉወርቅ
Comments