በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የውጭ ምንዛሪን ወደ ኢትዮጵያ ሲልኩ በአነስተኛ የመላኪያ ዋጋ እና በሰከንዶች ገንዘቡ ለተላከለት ደንበኛ እንዲደርስ የሚያስችል አዲስ ቴክኖኖሎጂ አሰናድቻለሁ ሲል የኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ ተናገረ፡፡
በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን በአነስተኛ የመላኪያ ዋጋ እና በቅፅበት ለተቀባይ እንዲደርስ በብሎክ ቼን ቴክኖሎጂ የታገዘ የሬሚታንስ(የሀዋላ) አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅቴን ጨርሼ ወደ ስራ ገብቻለሁ ብሏል፡፡
ባንኩ አገልግሎቱን የሚሰጠው በአለም አቀፍ ደረጃ በአካታች ፋይናንስና ማህበራዊ ተሳትፎ ላይ ከሚሰራው InFTF ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በጋራ በመሆን ነው የተባለ ሲሆን ወጭ ቆጣቢ፣ ቀላል እና ተደራሽ ነው ተብሏል።
በአፍሪካ ቴክኖሎጂውን መጠቀም የጀመረው የመጀመሪያው ባንክ ነው የተባለው የኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ ከዚህ ቀደም በሀዋላ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋለውን ችግር ይፈታል ተብሎ ታምኖበታል፡፡
ከዚህ በፊት በሀዋላ ከውጭ የሚላከው የገንዘብ መጠን ከፍተኛ ገንዘብ ካልሆነ መላክ እንደማይችል የተነገረ ሲሆን አሁን ባንኩ ወደ ስራ ያስገባው ቴክኖሎጂ ግን ከ1 ዶላር ጀምሮ መላክ የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ዲያስፖራዎች አነስተኛ ከሆነ የገንዘብ መጠን እስከ ከፍተኛ ፈንድ በተመጣጣኝ ክፍያ ከ3 ሰከንድ ባልበለጠ ጊዜ ለተጠቃሚው እንዲደርስ የሚያደርግ ነው የተባለለት በብሎክ ቼን ቴክኖሎጂ የታገዘው የሬሚታንስ ወይም የሀዋላ አገልግሎት ከሬሚታንስ መላኪያ ክፍያ ከፍተኛ መሆን ጋር በተገናኘ ገንዘብ መላክ ላይ የነበረውንም ውስንነት ያስቀራል፡፡
በተጨማሪም በክፍያ መወደድ፣ ገንዘቡ የተላከለት ደንበኛ ጋር በአጭር ጊዜ አለመድረሱ እና ሌሎችም ችግሮች ታክለውበት የኢትዮጵያ ዲያስፖራዎች በጥቁር ገበያ ዶላር ይልካሉ የተባለ ሲሆን ቴክኖሎጂው ወደ ስራ ሲገባ ግን ይህንን ሁሉ ችግር ይፈታል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡
ፋሲካ ሙሉወርቅ
Comments