አዋሽ ባንክ የስራ እድል ፈጠራን ለማበረታታት የጀመረውንና "ታታሪዎቹ "ሲል የጠራውን ውድድር ሁለተኛውን ዙር መጀመሩን ተናገረ።
የአዋሽ ባንክ የታታሪዎቹ ውድድር አዳዲስ የስራ ፈጠራ ክህሎት ኖሯቸው በፋይናንስ እጥረት ምክንያት መስራት ያልቻሉ ስራ ፈጣሪዎችን ለማበረታታት የታሰበ ነው፡፡
ስራ ፈጣሪዎቹ በውድድሩ ሲሳተፉ እንዲሁም ሲያሸንፉ ክህሎታቸው እንዲያድግ ስልጠና ያገኛሉ፣ የስራ መነሻ ካፒታልና የዘላቂ ብድር አቅርቦት ይሰጣቸዋል ሲል ባንኩ አስረድቷል።
የመጀመሪያው ዙር ውድድር ከግንቦት 8/2014ዓ.ም ጀምሮ ለ1 ዓመት ሲካሄድ ቆይቶ መጠናቀቁ ይታወሳል።
በመጀመሪያው ዙር ውድድር ላይ 8,000 ሰዎች ተመዝበው 1,200ዎቹ ተመርጠው የክህሎት ስልጠና ሲያገኙ ፣ ሲወዳደሩ ቆይተው የመጨረሻዎቹ 5ቱ የምስክር ወረቀት እና ከ200,000-1ሚሊዮን ብር መሸለማቸው ይታወሳል፡፡
አሸናፊዎቹ ከዚህ በተጨማሪም ስራቸውን የሚያቃኑበት ብድር ያለ ማስያዣ እንዲያገኙ ባንኩ ፈቅዶላቸዋል፡፡
በህክምና ፣ በግብርና ፣ በትራንስፖርት እና በሌሎች ዘርፎች የስራ ፈጠራ ሀሳብ ተወዳድረው ነው ያሸነፉት፡፡
በዛሬው ዕለት በባንኩ ዋና መ/ቤት በተካሄደው ሁለተኛው ዙር የስራ ፈጠራ ውድድር ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት ላይ የባንኩ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ፀሀይ ሽፈራው የሁለተኛው ዙር መርሃ ግብርም ዓላማ እንደኛው ዙር ሁሉ አዳዲስ የስራ ፈጠራ ባለቤቶችን ለማበረታታት የታሰበ መሆኑን አስረድተዋል።
በዚህ የስራ ፈጠራ ውድድር ላይ አዳዲስ እና ችግር ፈቺ የሆኑ የስራ ሀሳቦች ያላቸው በሁሉም የአገሪቱ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች መሳተፍ ይችላሉ ተብሏል።
ተወዳዳሪዎች የሥራ ፈጠራ ሃሳባችሁን በአማርኛ፣በኦሮሚኛ ወይንም በእንግሊዝኛ ቋንቋ ማቅረብ ትችላላችሁ ተብላችኋል፡፡
በውድድሩ ለመሳቸፍ የሚትፈልጉ ከጥቅምት 12-ህዳር 13፣2016 ዓ.ም ከባንኩ ድህረ-ገፅ እና ማህበራዊ ትስስር ገጾች እንዲሁም ወደ ሁሉም የባንኩ ቅርንጫፎች በመሄድ ቅፁን በመሙላት መወዳደር ትችላላችሁ ተብሏል።
Comentários