የፊታችን ቅዳሜ በአዲስ አበባ፣ በማግስቱ እሁድ ደግሞ በቢሾፍቱ ለሚከበረው የኢሬቻ በዓል አስፈላጊ ዝግጅቶች ተደርገዋል ተባለ።
የኦሮሚያ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ ሃይሉ አዱኛ የተደረጉ ዝግጅቶችን አስመልክተው ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸው እንዳሉት በዓሉ እሴቱን ጠብቆ በሠላም እንዲከበር በየደረጃው ያሉ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ውይይት አካሂደዋል።
የክልሉ፣ የአዲስ አበባ እና የፌዴራል የፀጥታ አካላትም በዓሉ በሠላም እንዲከበር ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን ተናግረዋል።
የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የሚሰጡ ወጣቶች እንዲሁ ህዝቡን ለማስተባበር እና ለመርዳት ተዘጋጅተዋል ብለዋል።
የአዲስ አበባ፣ የሸገር ከተማ እና የቢሾፍቱ ከተማ ነዋሪዎችም እንግዶችን ለመቀበል ዝግጅት እንደጨረሱ አቶ ሃይሉ ተናግረዋል።
በዓሉ ወደ ሚከበርባቸው ቦታዎች የየትኛውንም ፖለቲካ ፓርቲ አርማ ይዞ መሄድ በጥብቅ የተከለከለ መሆኑ በመግለጫው ወቅት ተነግሯል።
ከፀጥታ አካላት እና የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከሚሰጡ ወጣቶች ጋር መተባበር እንደሚያስፈልግም በኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ቢሮ ግቢ ውስጥ በተሰጠው በዚሁ መግለጫ ላይ ተነስቷል።
በዚህ መልኩም በዓሉ በሠላም ተጀምሮ በሠላም እንዲጠናቀቅ ሁሉም የበኩሉን ሃላፊነት እንዲወጣ የቢሮ ሃላፊው ጥሪ አቅርበዋል።
ንጋቱ ረጋሣ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… https://bit.ly/33KMCqz
Comments