በተለያየ የአለም ሀገራት የሚኖሩ እና የሌላ ሀገር ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ቀዳሚ ጥያቄያቸው ከኢትዮጵያ ጥምር ዜግነት ማግኘት ነው ተባለ፡፡
ይህን ያለው የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበር ነው፡፡
በተለያየ የአለም ክፍል የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ጥምር ዜግነት በኢትዮጵያ እንዲፈቀድ ጥያቄ ማቅረባቸውን የዲያስፖራ ማህበር ተናግሯል፡፡
ዲያስፖራው በሀገሩ ጉዳይ የመምረጥ፣ የመመረጥ መብት እንዲኖረው ይፈልጋል ሲሉ የነገሩን የማህበሩ ምክትል ፕሬዘዳንት ደመቀ ነጋሣ፤ ለዚህም ኢትዮጵያ የጥምር ዜግነት እንድትፍቅድ በማህበሩ በኩል ለመንግስት ጥያቄ ቀርቧል ብለውናል፡፡
በሌላ በኩል በመላው አለም የሚገኙ የሀገር ልጆች በሃገራቸው ጉዳይ ያገበኛል ብለው እውቀታቸው፣ ጉልበታቸው ገንዘባቸው ለሀገራቸው እንዲያደርጉ ያግዛል የተባለ የዲያስፖራ ሳምንት መዘጋጀቱን ሰምተናል፡፡

የዲያስፖራ ሳምንቱ በገና በዓል ሰሞን በአዲስ አበባ፣ በካናዳ ቶሮንቶ ኤግዚብሽን ሲንፖዚየም፣ የእራት ግብዣ እንዲሁም ታላቅ የዲያስፖራ ሩጫ ያካተተ መሆኑን የማህበሩ ምክትል ፕሬዘዳንት ነግረውናል፡፡
በእነዚህ ዝግጅቶች ዲያስፖራዉ በሀገሩ እንዲሰራ የፖሊሲና የአሰራር ማነቆዎች የተሻለ መፍትሔ እንዲኖር ከሚመለከታቸዉ አካላት ጋር በቅርበት መስራት፣ ዲያስፖራዉ ለሚፈልገው የኢንቨስትመንትና መሰል ጉዳዮች ድጋፍ ሲያስፈልገው ተገቢዉን ድጋፍ መስጠት፣ ለሀገሩ ጉዳይ ጉልህ ተሳትፎ እንዲኖረው ማስቻልና የመሳሰሉት ቁልፍ ጉዳዮች ይሰራባቸዋል ተብሏል፡፡
በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵዊያን በሀገራቸው መጥተው ገንዘባቸው፣ እውቀታቸው ስራ ላይ እንዲውል በተደጋጋሚ ጥሪ ሲቀርብላቸው ይሰማል፡፡
በሌላ በኩል ግን የሀገሪቱ ቢውሮክራሲ፣ ተገማች ያልሆነ የህጎች መለዋወጥ እና የፀጥታ ችግር በዲያስፖራው በኩል ይነሳል፡፡
የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበር እነዚህ ችግሮች እንዲፈቱ ምን ሰራ ምንስ የተለወጠ ነገር አለ ያልናቸው አቶ ደመቀ ነጋሣ ብዙ ነገር ተለውጧል ይላሉ፡፡
ንጋቱ ሙሉ
Comentarios