top of page

መስከረም 22፣2017 - በአማራ ክልል ከዓመት ዓመት የወባ ወረርሽኝ እየጨመረ ነው ተባለ፡፡

ካሳለፍነው ሀምሌ ወር 2016 ዓ.ም ጀምሮ 415,000 በላይ ሰዎች በወባ የተያዙ መሆናቸውን ሪፖርት ያሳያል ብሏል የክልሉ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፡፡


የአዊ ዞን፣ የደቡብ ጎንደር ዞን፣ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን፣ የምዕራብ እና ምስራቅ ጎጃም፣ ምዕራብ ጎንደር ዞኖች በቅደም ተከተላቸው ወረርሽኙ ከፍተኛ ስርጭት የሚታዩባቸው አካባቢዎች ናቸው ይላሉ የኢንስቲትዩቱ የወባ መከላከል እና መቆጣጠር ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ዳምጤ ላንክር፡፡

አሁን በክልሉ ያለው የወባ ወረርሽኝ ካለፉት አምስት ዓመታት ጋር ሲነፃፀር ጭማሬ ማሳየቱን የሚናገሩት አቶ ዳምጤ ከአመት አመት ከፍ እያለ ነው ይላሉ፡፡


በአማራ ክልል ብቻ አይደለም እንደሀገር የወባ ወረርሽኝ እየጨመረ መጥቷል የሚሉት ፕሮግራም አስተባባሪው የአየር ንብረት ለውጥ፣ ከግንዛቤ መፍጠር ጋር በተገናኘ ጠንካራ ስራ አለመሰራቱ፣ የማህበረሰቡ የአጎበር አጠቃቀም ዝቅተኛ መሆን እና ሌሎችም ምክንያቶች አሁን ላለንበት የወረርሽኝ መጨመር እንደ ምክንያት የሚነሱ ናቸው ብለዋል፡፡


ክልሉ አሁን የገጠመውን የወባ ወረርሽኝ ለመቆጣጠር የሚያስችለው በቂ የመድሃኒት አቅርቦት አለው የሚሉት የወባ መከላከል እና መቆጣጠር ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ዳምጤ ነገ እና ከነገ በስቲያ ወረርሽኙ የሚቀጥል ከሆነ አቅም አይኖረንም ይላሉ፡፡


መጭው ወራትም ውሀ ሊያቁሩ የሚችሉ ቦታዎች መጨመራቸውን ተከትሎ ለወባ ወረርሽኝ ከፍ ማለት አመች ጊዜ ይፈጥራል ይህ ደግሞ ለኛ ስጋ ሆኖብናል ብለዋል፡፡


በክልሉ ለወባ ስርጭት አመች ናቸው የተባሉት ወረዳዎችን በመለየትም የግንዛቤ ስራ እና ሌሎች የመከላከያ ተግባሮችን እየሰራን ነው ሲሉ ለሸገር ራዲዮ ተናግረዋል፡፡


ቀድሞውኑ እንደ ስኳር፣ ደም ግፊት እና ሌሎች በሽታዎች ያሉባቸው እና በወባ በሽታ የተያዙ 31 የሚሆኑ ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉን አቶ ዳንጤ ላንክር ተናግረዋል፡፡





ፋሲካ ሙሉወርቅ

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page