top of page

መስከረም 20፣2017 - ገደብ አልባ የነበረውን በፖሊስ የሚጠየቀው 14 ቀን የምርመራ የጊዜ ቀጠሮ ገደብ እንዲኖረው ሆኖ ህጉ እየተሻሻለ መሆኑ ተሰማ

በወንጀል ህጉ እስካሁን ገደብ አልባ የነበረውን በፖሊስ የሚጠየቀው 14 ቀን የምርመራ የጊዜ ቀጠሮ ገደብ እንዲኖረው ሆኖ ህጉ እየተሻሻለ መሆኑ ተሰማ፡፡


ወንጀል ሰርቷል ተብሎ የተጠረጠረና በህግ ቁጥጥር ስር የዋለ ግለሰብ ሰርቷል ስለ ተባለው ወንጀል ማስረጃ ለማሰባሰብ በሚል #መርማሪ_ፖሊስ በያዘው ተጠርጣሪ ላይ ምርመራ ለማድረግ ፍርድ ቤትን በተደጋጋሚ የምርመራ ጊዜ ሲጠይቅ ይስተዋላል።


በስራ ላይ ባለው #የወንጀል_ሥነ_ሥርዓት_ሕግ መደበኛው በሚባለው ወንጀል የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ መጠየቅ ይቻላል፡፡


ግለሰቡ በፀረ-ሽብር ወንጀል ተከስሶ እንደሆነ የ28 ቀን የምርመራ ጊዜ ሊፈቀድ እንደሚችል ያስቀምጣል።


ነባሩ ሕግ ዳኛው የጊዜ ቀጠሮን ያለ ገደብ እንዲሰጥ ይፈቅዳል።


ከ60 ዓመታት በላይ ስራ ላይ የቆየውን የወንጀል ህግ ለማሻሻል በረቂቅ ደረጃ ያለው አዲሱ ህግ ግን 14 ቀን፣ 28 ቀን እየተባለ የሚፈቀደው የጊዜ ቀጠሮ ገደብ እንዲኖረው ያስችላል፡፡


አዲሱ ህግ ምን ምን ያካትታል?


በህጉ ለወንጀሎቹ ዝቅተኛ ወንጀል፣ መካከለኛ ወንጀል እና ከፍተኛ ወንጀል የሚል ደረጃ በማውጣት የምርመራ ቀን ብዛት እና ገደብ ላይ ጣራ ያስቀምጣል።


መካከለኛ ለሚባሉ ወንጀሎች መርማሪ ፖሊስ ከሁለት ጊዜ በላይ የምርመራ ጊዜ መጠየቅ አይችልም።


በተቻለ መጠን አንድ ተጠርጣሪ ከመያዙ በፊት ፖሊስ ማስረጃ እንዲሰበሰብ ያደርጋል።


ተጠርጣሪው ምርመራ እየተደረገበት እንደሆነ አውቆ አራሱን ለመሰወር እና ማስረጃ ለማጥፋት የሚሞክርበት ሁኔታ እስካልተፈጠረ ድረስ፣ ፖሊስ የምርመራ ስራውን ጨርሶ ተጠርጣሪውን እንዲይዝ ሚያደርግ፣ ተጠርጣሪን ይዞ ማስረጃ የመፈለግ አሰራር እንዲቀየር እድል የሚፈጥር ነው።


‘’አሁን ባለው ሁኔታ 14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ የሚፈቀደው ያለገደብ በመሆኑ መርማሪ ፖሊሶች ያለ አግባብ ይጠቀሙበታል፤ አንድ እና ሁለት ቀን ለሚፈጅ ምርመራ 14 ቀን በተደጋጋሚ ይጠይቃሉ፤ ዳኞችም ብዙ ጊዜ የጊዜ ቀጠሮውን የሚፈቅዱት ጉዳዩን ሳያጤኑ ነው’’ የሚሉት ያነጋገርናቸው የደብረ ታቦር ዩንቨርሲቲ የህግ መምህርና ጠበቃው አቶ መሳፍንት አላቸው ናቸው፡፡


‘’የጊዜ ቀጠሮን ጉዳይ በህጉ እንዲወስኑ የተሰጠው ለዳኞች ነው፤ ዳኞች በሚወስኑት ፍትሃዊነት የጎደለው ውሳኔ ሰዎች ያለ አግባብ ይታሰራሉ፣ በአጭር ጊዜ ማለቅና የፍርድ ውሳኔ ማግኘት ያለበት ተጠርጣሪ በየ14 ቀኑ ፍርድ ቤት እየቆመ ዓመታትን ያስቆጥራል፤ ግለሰቡ የተጠረጠረው በፖለቲካዊ ጉዳይ ከሆነ ደግሞ ችግሩን ያከፋዋል’’ ይላሉ።


ይህን መሰሉን አሰራር ይቀይረዋል የተባለው አዲሱ የወንጀል ሥነ ሥርዓት ህግ በረቂቅ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡


ሙሉ ዘገባውን በድምፅ ለማድመጥ ይህንን ማስፈንጠሪያን ይጫኑ… https://tinyurl.com/383bbn4d


ምንታምር ፀጋው

Commentaires


bottom of page