በሳውዲ አረቢያ ጄዳ የሚገኘው ታላቁ ገበያ ተቃጠለ፡፡
ገበያው ቀኑን ሙሉ ሲጋይ መዋሉን አረብ ኒውስ ፅፏል፡፡
ቃጠሎው መጠነ ሰፊ ቁሳዊ ውድመት አስከትሏል ተብሏል፡፡
በሰዎች ላይ ስለደረሰ ጉዳት የተጠቀሰ ነገር የለም፡፡
ቃጠሎው በቁጥጥር ስር የዋለው ከ12 ሰዓታት ርብርብ በኋላ መሆኑ ታውቋል፡፡
ቃጠለው እንደተቀሰቀሰ እሳቱ በፍጥነት መዛመቱ ተሰምቷል፡፡
የቃጠሎው መንስኤ ምን እንደሆነ ለጊዜው የታወቀ ነገር የለም፡፡
ምርመራ ግን ይከናወናል ተብሏል፡፡
የእስራኤል ጦር በአርብ እለቱ የቤይሩት የአየር ድብደባዬ ከሔዝቦላሁ የበላይ ሐሰን ናስረላህ ጋር 20 የቡድኑን ከፍተኛ ሹሞች ገድያለሁ አለ፡፡
ሔዝቦላህም በአርብ እለቱ ጥቃት የደቡባዊው ግንባር አዛዥ ዓሊ ካራኪ መገደሉን እንዳመነ ቢቢሲ ፅፏል፡፡
እስራኤል ባለፈው ሳምንት የጀመረችውን ከባድ የአየር ድብደባ ትናንትናም መቀጠሏ ታውቋል፡፡
ትናንትናም ከቤይት በስተደቡብ የሚገኘው የከተማዋ ክፍል በጦር አውሮፕላኖች በተደጋጋሚ መደብደቡ ተሰምቷል፡፡
በሰሜናዊ ምስራቅ የአገሪቱ ክፍል የሚገኘውም የቤካ ሸለቆ የእስራኤል የድብደባ ዒላማ ነበር ተብሏል፡፡
እስራኤል የሊባኖስ የአየር ድብደባዋን አድማስ እያሰፋችው መሆኑ በመረጃው ተጠቅሷል፡፡
ሐማስ በሊባኖስ የቡድኑ መሪ ሆኖ የቆየው ፋታህ ሸሪፍ አቡ ኤል አሚን በእስራኤል የአየር ድብደባ መገደሉን እወቁልኝ ብሏል፡፡
PFLP የተሰኘው የፍልስጤም ታጣቂ ቡድን መሪዎችም ሊባኖስ ውስጥ መገደላቸው ተሰምቷል፡፡
የሊባኖሱ ባለአደራ ጠቅላይ ሚኒስትር ናጂብ ማካቲ በእስራኤል ድብደባ እየከፋ መምጣት የተነሳ 1 ሚሊዮን ያህል ሊባኖሳውያን ለመፈናቀል ተዳርገዋል አሉ፡፡
የእስራኤል የአየር ድብደባ ካለፈው ሳምንት ሰኞ አንስቶ እየከፋ ቢመጣም ጥቃቷ አስቀድሞ መጀመሩን ሚድል ኢስት ሞኒተር አስታውሷል፡፡
የሊባኖሳውያን ስደት እና መፈናቀል ሊብስ እንደሚችል ባለአደጋው ጠቅላይ ሚኒስትር ተናግረዋል፡፡
እንደውም ስደት እና መፈናቀሉ ሊባኖስ በታሪኳ ገጥሟት የማያውቅ ዓይነት ሊሆን ይችላል ብለዋል፡፡
በእስራኤል የሰሞኑ ድብደባ ከ800 በላይ ሰዎች ሲገደሉ ከ2 ሺህ 500 የሚልቁት ደግሞ የተለያየ ደረጃ አካላዊ ጉዳት እንደገጠማቸው መረጃው አስታውሷል፡፡
እስራኤል በየመን የሁቲዎቹን ይዞታ በጦር አውሮፕላኖች ደበደበች፡፡
የሁዴይዳን እና የአል ኢሳ ወደቦች ዋነኞቹ የእስራኤል የድብደባ ዒላማዎች እንደነበሩ አረብ ኒውስ ፅፏል፡፡
የነዳጅ ማጠራቀሚያዎችም ተመትተዋል ተብሏል፡፡
የሁዴይዳ ዋነኛ የሀይል ማመንጫም መደብደቡ ተጠቅሷል፡፡
ቻይና ኦርግ እንደፃፈው በእስራኤል የየመን ድብደባ 4 ሰዎች ሲገደሉ 50 ያህሉ ደግሞ አካላዊ ጉዳት ገጥሟቸዋል፡፡
እስራኤል በየመን ከባድ የአየር ድብደባ የፈፀመችው ሰሞኑን ሁቲዎቹ በእስራኤል ላይ የሚሳየል እና የድሮን ጥቃቶችን ከሰነዘሩ በኋላ ነው ተብሏል፡፡
ሁቲዎቹ እስራኤል የጋዛ እና የሊባኖስ ጥቃቷን ካላቆመች አንለቃትም እያሉ ነው፡፡
ሰንዓን ጨምሮ የመንን ሰሜናዊ ክፍል የሚያስተዳድሩት ሁቲዎቹ የኢራን ሁነኛ ፖለቲካ አጋሮች እና የጦር ሸሪኮች እንደሆኑ ይነገራል፡፡
የኔነህ ከበደ
Comentários