በአዲስ አበባ ከተማ ከኮሪደር ልማቱ በኋላ ዘምባባ መግጨት 300,000 ብር እያስቀጣ መሆኑ ተነግሯል፡፡
የተቀጡ አሽከርካሪዎችም መኖራቸው ተዘግቧል፡፡
የደንብ ማስከበር ባለስልጣን ቅጣት ማስከፈል የሚችለው በደንቡ መሰረት እስከ 100,000 ብር ብቻ ነው፡፡
ለመሆኑ ቅጣቱን የሚያስፈፅመው ማን ነው? በየትኛው ህግ ለሚለው እስካሁን ግልፅ ያለ ነገር የለም፡፡
ሸገር የጠየቃቸው ተቋማትም እርስ በርስ በመገፋፋት እኔን አይመከትም የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ለመሆኑ ባልተፃፈ መመሪያ ቅጣቱ እየተላለፈ ከሆነ በህግ ዓይን እንዴት ይታያል?
ለዘንባባ 300,000 ብር ቅጣት እንዲጣል ህግ አለው ወይ? ስንል የጠየቅነው የከተማዋ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ‘’ተመኑን የሚያወጣው ፖሊስ ኮሚሽን ነው እሱን ጠይቁ’’ ብሏል፡፡
ፖሊስ ኮሚሽን ‘’አይመመከተኝም የትራፊክ ማኔጅመንትን ጠይቁ’’ የሚል ምላሽ ሰጠን፡፡
ትራፊክ ማኔጅመንትም ‘’ጉዳዩ አይመለከተኝም’’ ብሏል፡፡
በርከት ያለ ዘንባባ በተሽከርካሪ ተገጭቶ ቅጣት የተላለፈው በቦሌ ክፍለ ከተማ እንደመሆኑ የክፍለ ከተማውን ደንብ ማስከበር ፅ/ቤት ጠይቀናል፡፡
ቅጣቱ መተላለፉን ጠቅሶ ‘’ተመኑን የሚያወጣው የከተማዋ የአረንጓዴ ልማት ተፋሰስ ነው’’ ብሎናል፡፡
በዚሁ ሁሉ ሂደት ለዘንባባ መግጨት 300,000 ብር የሚያስከፍል ቅጣት ስለመሆኑ የተፃፈው ህግ የጠቀሰልን ተቋም ማግኘት አልቻልንም፡፡
ትዕግስት ዘሪሁን
Comments