top of page

መስከረም 2፣2016 - የባህር ማዶ ወሬዎችከባድ አውሎ ናፋስ እና ጎርፍ መጠነ ሰፊ ጉዳት ያደረሰባት ሊቢያ ለ3 ቀናት የሚዘልቅ ብሔራዊ ሐዘን ላይ ነች፡፡


ከባዱ ዶፍ ዝናብ ያስከተለው ጎርፍ ከ5 ሺህ በላይ ሰዎችን እንደገደለ TRT ዎርልድ ፅፏል፡፡


ከ10 ሺህ የሚለቁ ሰዎች ደግሞ የደረሱበት እንዳልታወቀ ሹሞች ተናግረዋል፡፡


በምስራቃዊ የአገሪቱ ክፍል የምትገኘው ዴርና ከተማ በአደጋው ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሳባት ታውቋል፡፡


ከባዱ ጎርፍ ግድቦችን ደረማምሷል ፤ ድልድዮችንም ማፈራረሱ ተሰምቷል፡፡


የግድቦቹ መደርመስ የጎርፍ አደጋውን አባብሶታል ተብሏል፡፡ሰሜን ኮሪያ ሁለት የባልስቲክስ ሚሳየሎችን መተኮሷ ተሰማ፡፡


እስያዊቱ ሀገር የባልስቲክ ሚሳየሎቹን የተኮሰችው መሪዋ ኪም ጆንግ ኡን በሩሲያ በጉብኝት ላይ በሚገኙበት አጋጣሚ እንደሆነ RFA በድረ ገፁ ፅፏል፡፡


ሚሳየሎቹ የተተኮሱት ወደ ምስራቃዊው የባህር ክፍል መሆኑ ታውቋል፡፡


ኪም ጆንግ ኡን ከሩሲያው ፕሬዘዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በሩሲያ ሩቅ ምስራቅ ተገናኝተው መነጋገራቸው ተሰምቷል፡፡


የሩሲያው ፕሬዘዳንት ሀገራቸው ሰሜን ኮሪያን በሳታላይት ግንባታ እንደምትረዳት ለኪም ጆንግ ኡን ቃል ገብተውላቸዋል ተብሏል፡፡


የዩክሬይኑ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዲህ ሰሜን ኮሪያ ከሩሲያ ሁነኛ ወዳጆች አንዷ ሆና ትቆጠራለች፡፡


ኪም ጆንግ ኡን አሁንም ከሩሲያ ጎን ነን ማለታቸው ተሰምቷል፡፡


ምዕራባዊያን ሰሜን ኮሪያ ለሩሲያ ጥይቶችን ልታቀብል ትችላለች የሚል ስጋት እንደገባቸው ዘገባው አስታውሷል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን በሚጠብቃቸው ክስ በህዝብ ተወካዮቹ ምክር ቤት ኮሚቴ ሊጠየቁ ነው ተባለ፡፡


የህዝብ ተወካዮቹ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ኬቪን ማካርቲ ፕሬዘዳንቱን እንዲመረመሩ የሚመለከተውን ኮሚቴ አዛለሁ ማለታቸውን TRT ዎርልድ ፅፏል፡፡


ባይደን የሚመረመሩት ስልጣንን አለ አግባብ በመገልገል፣ ፍትህን በማዛባት እና በምዝበራ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡


ኪቨን ማካርቲ ፕሬዝዳንቱን ሊያስከስሱ የሚሉ ፍንጮች አሉ ማለታቸው ተሰምቷል፡፡


የህዝብ ተወካዮቹ ምክር ቤት ባይደን እንዲከሰሱ ከወሰነ ጉዳዩ ወደ ህግ መወሰኛ ምክር ቤቱ /ሴኔት/ ማምራቱ አይቀርም ተብሏል፡፡


ይሁንና ሴኔቱ ዴሞክራቶች የሚበዙበት በመሆኑ ፕሬዘዳንቱን ከስሶ ከሀላፊነት የማስነሳቱ ጉዳይ እድሉ የጠበበ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡


እስካሁን ጉዳዩ ሴኔቱ ጋር ደርሶ ከሀላፊነት የተነሳ አንድም ፕሬዘዳንት እንዳልነበረ ዘገባው አስታውሷል፡፡ቱርክ እና ጣሊያን ሊቢያን ለመርዳት እየፈጠኑላት ነው፡፡


ሁለቱ ሀገሮች በከባድ አውሎ ነፋስ እና ጎርፍ መጠነ ሰፊ ጉዳት ለደረሰባት ሊቢያ እርዳታ ለማቅረብ ቀዳሚዎቹ እንደሆኑ ቢቢሲ ፅፏል፡፡


የሊቢያ ቀይ ጨረቃ ማህበር በአደጋው ምክንያት አገሪቱ ከፍተኛ ሰብአዊ እርዳታ እንደሚያሻት እወቁልኝ ማለቱ ተሰምቷል፡፡


ኢራንም ለሊቢያ እርዳታ ለማቅረብ አይዞሽ እንዳለቻት ታውቋል፡፡


የቴሕራንን እርዳታ በመቀበል በኩል ከሊቢያ ሹሞች የተሰጠ ምላሽ በዘገባው አልተጠቀሰም፡፡


ሁለቱ አገሮች ተቋርጦ የቆየውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ለማደስ የተስማሙት በቅርቡ እንደሆነ መረጃው አስታውሷል፡፡
የአለማችን አነስተኞቹ ደሴታማ አገሮች ከመጥፋት አደጋ ልንጠበቅ ይገባል ሲሉ ለተባበሩት መንግስታት ፍርድ ቤት አቤቱታ አቀረቡ፡፡


የተባበሩት መንግስታት የባህር ህግ ፍርድ ቤት ማስቻያው በጀርመን ሐምበርግ ነው፡፡


ባለ አነስተኛ ደሴቶቹ አገሮች በአየር ለውጥ ምክንያት የባህር ከፍታ እየጨመረ በመምጣቱ የመዋጥ ስጋት ተጋርጦብናል ብለዋል በማመልከቻቸው፡፡


ለአየር ለውጡ ደግሞ ታላላቆቹ አገሮች የሚለቁት በካይ ጋዝ ዋነኛው ምክንያት ሆኖ ይቀርባል፡፡


በአለም ላይ ከሚለቀቀው በካይ ጋዝ 25 በመቶው በውቅያኖሶች ይሳባል ይባላል፡;


በዝቅተኛ ስፍራ የሚገኙ የአነስተኞቹ ደሴታማ ሀገሮች መንግስታት በዚህ ምክንያተ በባህር ውሃ ከፍታ ከመጥለቅለቅ አደጋ ልንጠበቅ ይገባል ማለታቸው ተሰምቷል፡፡


ይሁንና ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ቢያሳልፍ እንኳ ትዕዛዙ አስገዳጅነት እንደማይኖረው ዘገባው አስታውሷል፡፡
የኔነህ ከበደ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… https://bit.ly/33KMCqz

Comments


bottom of page