top of page

መስከረም 13፣2017 - ወርሃ መስከረም የኢትዮጵያ አስጎብኚ ማህበራት ቱሪስቶች ይዘው ወደ ተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍል የሚንቀሳቀሱበት ወቅት ነበር

አዲስ ዓመት፣ መስቀል፣ ኢሬቻ ፣ እና ሌሎች ሀይማኖታዊና ባህላዊ የአደባባይ በዓላት የሚከበሩበት ጊዜ ነው፡፡


በዚህም ምክንያት የውጪ ሀገራት ቱሪስቶችና የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች ከቦታ ወደ ቦታ የሚጓጓዙበት፣ ጎብኚውም፣ አስጎብኚውም እንዳሻው የኢትዮጵያን ጋራ ሸንተረር፣ ታሪክና ቅርስ የሚመለከቱበት መስከረም አሁን ተቃራኒው ሆኗል ተብሏል፡፡


የውጪ ሀገራት ጎብኚዎች ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት የሚፈሩበት የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች ከቦታ ወደ ቦታ ለመንቀሳቀስ የሚሰጉ ሆነዋል ይላሉ የዘርፉ ባለሞያዎች፡፡


ይህንን የሰማነው የኢትዮጵያ ቱሪስት አስጎብኚ ባለሙያዎች ማህበር በአዲስ አበባ ሙዝየም ለ3 ተኛ ጊዜ ባዘጋጀው የፎቶ አውደርዕይ ላይ ነው፡፡

አሁን ባለው የሀገር ውስጥ ግጭት ዘርፉ ከሌሎች ጊዜያት እጅጉኑ ተቀዛቅዟል ያሉን የቱሪዝም ባለሙያው አቶ ዮሃንስ ዋሴ ናቸው፡፡


ከዚህ በፊት መስቀል ሲደርስ አስጎብኚው ስራ ይበዛበት ነበር የሚሉት ባለሙያው አሁን ግን ነገሮች በተቃራኒው እየሆኑ ነው ሲሉ ያስረዳሉ፡፡


የኢትዮጵያ ቱሪስት አስጎብኚ ባለሙያዎች ማህበር የቦርድ አባል የሆኑት አቶ ዮናስ ምትኩ በበኩላቸው ሰላም መታጣቱ የውጪ ሀገራት ቱሪስቶች እንዲርቁ እያደረገ ነው ብለዋል፡፡


አሁን ወደ ሀገር ቤት የሚመጡት የውጪ ሀገራት ጎብኚዎች የሚገኙት አስጎብኚ ማህበራት በሚያደርጉት የማግባባት ስራ ነው ያሉት አቶ ዮናስ ጎብኚዎቹ ወደ ኢትዮጵያ ከመጡም በኋላ የሰላም እጦት ወዳለባቸው አካባቢዎች መሄድ አይፈልጉም ሲሉ ነግረውናል፡፡


በተለያዩ ጊዜያት የውጪ ሀገራት ጎብኚዎች ኢትዮጵያ መጥተው ካዩ በኋላ ያለው ሀብት ተመልክተው ሀገራችሁን ለምን አታስተዋውቁም እያሉ ይጠይቁናል ብለዋል አቶ ዮናስ፡፡


ተፈጥሮ ስላለና የሚጎበኙ ቅርሶችን ስላሉን ብቻ ጎብኚ አይገኝም ያሉት አቶ ዮናስ ችግሮች እንዳሉ ሆኖም እራስን ለአለም ማስተዋወቅ ያስፈልጋል በማለት ይመክራሉ፡፡

የቱሪዝም ሚንስትር ዴዕታው አቶ ስለሺ ግርማ መንግስት ሰላም ያለባቸው አካባቢዎችን በመለየት የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎችን እያስተዋወቀ ነው ብለዋል፡፡


በተለይም በአካባቢዎቹ የተለያዩ ኩነቶች ሲካሄዱ ከዛው ጋር በማያያዝ ጎብኚዎች ወደ ስፍራው እንድሄዱ ለማድረግ እየተሞከረ መሆኑን አቶ ስለሺ ተናግረዋል፡፡


የኢትዮጵያ አስጎብኚ ባለሙያዎች ማህበር በ2016 በጀት አመት የማህበሩ አባላት የተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ሲዘዋወሩ ያነሷቸው ፎቶዎችን በመሰብሰብ የፎቶ አውደርዕይ አዲስ አበባ ሙዝየም ከመስከረም 11 እስከ መስከረም 13 ድረስ እያካሄደ ሲሆን ዛሬ ከሰዓት ፍፃሜውን ያገኛል፡፡


በረከት አካሉ

Commentaires


bottom of page