top of page

መስከረም 11፣2016 - አሜሪካን ሲሰልል ተገኝቷል የተባለው በዜግነት አሜሪካዊ በትውልድ ኢትዮጵያዊ የሆነው ግለሰብ ክስ ተመሰረተበት



በአሜሪካ መንግስት በኮንትራት ተቀጥሮ ይሰራ ነበር የተባለው አቶ አብርሃም ተክሉ ለማ፤ ሌላን የውጭ ሀገር መንግስት ለመጥቀም ሲል የአሜሪካን የደህንነት መረጃዎች አሳልፎ ሰጥቷል የሚል ክስ ቀርቦበታል፡፡


አቶ አብርሃም በወንጀሉ ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር የዋለው ባለፈው ነሐሴ 18 ቀን 2015 ዓ.ም ሲሆን እ.ኤ.አ ከዴሴምበር 2022 እስከ ኦገስት 2023 ድረስ የተለያዩ መረጃዎችን ለሌላ ወገን አቀብሏል ተብሏል፡፡


ከአሜሪካ ውጭ የሆነን መንግስት ለማገዝ፤ አቶ አብርሃም የተለያዩ መረጃዎችን ከደህንነት ሪፖርት ላይ በመውሰድ እና ጥብቅ ሚስጥር እና ሚስጥር ተብለው የተለዩበትን ምልክት በማጥፋት አሳልፎ መስጠቱ በክሱ ላይ ሰፍሯል፡፡


የአሜሪካ የፍትህ ሚኒስቴር ባወጣው መረጃ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኮፒ በማድረግ አሳልፎ ሰጥቷቸዋል የተባሉ ሰነዶች ስለ አንድ ሀገር ወይም ስለ ቀጠናዊ ሁኔታ የሚለግልጹ የሳታላይት ምስሎችንና ሌሎች መረጃዎችን ያካተተ ነው፡፡


አቶ አብርሃም መረጃውን አሳልፎ ሰጥቷል ከተባለው የውጭ ሀገር የደህንነት አገልግሎት ባለስልጣን ጋር በነበረው ግንኙነት መረጃዎቹን አሳልፎ በመስጠት ሃገሪቱን መርዳት እንደሚፈልግ መግለፁ ተረጋግጧል ቢባልም የሀገሪቱ ስም ግን በመረጃው አልተጠቀሰም፡፡


ከሌላ ሀገር የደህንነት ባለስልጣን ጋር ሲያደርገው ነበር በተባለው ግንኙነት፤ ባለስልጣኑ አሁን ጊዜው አቶ አብርሃም እርዳታቸውን መቀጠል ያለባቸው ጊዜ መሆኑን ሲገልፅ አቶ አብርሃምም “ተቀብያለሁ” ይገባኛል የሚል ይዘት ያለው ምላሽ ሰጥቷል ይላል መረጃው፡፡


የውጭ ሀገር የደህንነት መ/ቤት ባለስልጣን የተባሉት ግለሰብ መረጃ በማቀበሉ ሂደት በአንድ ጉዳይ ላይ ትኩረት ስለማድረጉ ጠቅሶ ሲያመሰግነው ፤ አቶ አብርሃም በዛው ሳምንት በጉዳዩ ላይ ትኩረት አድርጎ ስለመሰንበቱ መልስ ሰጥቷል ተብሏል፡፡


የወንጀል ክሱ እንደሚለው በስለላ የተከሰሰው አቶ አብርሃም የሳታላይት ምስሎችን፣ ማንነቷ ባልተጠቀሰ ሀገር እና ቀጠና ያለውን ወታደራዊ እንቅስቃሴ የተመለከቱ ሌሎች መረጃዎችን አሰልፎ ሰጥቷል፡፡


አቶ አብርሃም የተከሰሱበት የስለላ ወንጀል በአሜሪካ ህግ ከእድሜ ልክ እስራት እስከ ሞት የሚያስቀጣ መሆኑን መረጃው ጠቅሷል፡፡


የአሜሪካ የፌዴራል የምርመራ ቢሮ የዋሽንግተን ቅርንጫፍ፣ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የዲፕሎማሲ ደህንነት አገልግሎት እና የፍትህ ሚኒስቴር በጋራ ጉዳዩን እየመረመሩት ነው ተብሏል፡፡



ትዕግስት ዘሪሁን


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… https://bit.ly/33KMCqz

Kommentare


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page