ኢትዮጵያ እና ሶማሊያን ለማሸማገል በምታደርገው ጥረት ቱርክ በቅድሚያ ሁለቱን ሀገራት በተናጠል ልታነጋግር ነው፡፡
ከዚህ ቀደም ሁለት ጊዜ ለማሸማገል ያደረገችው ጥረት ውጤት ሳያመጣ ቀርቷል፡፡
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የገቡበት ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት በንግግር እንዲፈታ ባለፈው ማክሰኞም ለማሸማገል ቀጠሮ ተይዞ የነበረ ሲሆን ተራዝሟል መባሉ ይታወሳል፡፡
ይህን ተከትሎም ትናንት የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለአናዶሉ በሰጡት መግለጫ ከዚህ በኋላ ሁለቱን ሃገራት ፊት ለፊት አገናኝቶ ከማሸማገሏ በፊት ቱርክ ኢትዮጵያንም ሶማሊያንም ለየብቻቸው ለማነጋገር ውሳኔ ላይ ደርሳለች ብለዋል፡፡

ባለፈው ጥር ወር ሶማሊያ የግዛቴ አካል ነች ከምትላት ሶማሌላንድ ጋር በወደብ ጉዳይ የመግባቢያ ሰነድ መፈረሟን ተከትሎ ሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት ውስጥ መግባታቸው ይታወቃል፡፡
የቱርኩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካሃን ፊዳን እንዳሉት ቱርክ ችግሩ በሰላም እንዲፈታ ሁለቱንም ሀገራት በሚኒስትሮችና በከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች ደረጃ ማነጋገሯን ቀጥላለች፡፡
ሁለቱ ሀገራት በቀጥታ ፊት ለፊት ከመገናኘታቸው በፊት ወደ ሚያስማማ ነጥብ እስኪመጡ ድረስ በተናጠል እያነጋገርን እንቀጥላለን ብለዋል፡፡
ሶማሊያና ኢትዮጵያን ለማሸማገል የተራመዘው ሶስተኛው ዙር ንግግር መቼ ሊሆን እንደሚችል በመረጃው አልተጠቀሰም፡፡
ትዕግስት ዘሪሁን
Yorumlar