ሐምሌ 9፣ 2016 - ዩኒቨርሲቲዎች በሚገባቸው ልክ ለማህበረሰብ አገልግሎት እየሰጡ አይደለም ተብሏል
- sheger1021fm
- Jul 16, 2024
- 2 min read
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከተቋቋሙበት አንዱ አላማ፤ የማህበረሰብ አገልግሎት መስጠት ቢሆንም እምብዛም እየሰሩበት አይደለም፡፡
በተለይም ዩኒቨርሲቲዎቹ በተቋቋሙበት አከባቢ ከለው ማህበረሰብ ጋር ተቀራርበው እንዲሰሩና ለችግሮች መፍትሄ እንዲሰጡ ጥናትና ምርምር ያደርጋሉ ተብሎ ቢጠበቅም ኢትዮጵያ ውስጥ ይህ ሲሆን አይስተዋል ተብሏል፡፡
በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የዩኒቨርሲቲዎችና የማህበረሰብ ጉድኝትን በተመለከተ ኃሳባቸውን ያጋሩ ምሁራን እንደሚሉት ኢትዮጵያ ውስጥ የዩነቭስቲዎችና የማህበረሰቡ ጉድኝት በጣም ደካማ ነው ብለዋል፡፡
ለዚህም እንደ ምክንያት የተነሱ ሀሳቦች ተቀራርቦ አለመስራት ዩንቨርስቲዎች አካባቢ እኛ ብቻ እናውቃለን የሚል እሳቤ በመምህራን ዘንድ መኖሩ እና ባለሀብቱ ደግሞ ለምርምር ተቋሙ ራሱን ዝግ በማድረግ ድጋፍ መንፈጋቸው የሚሉት ተነስተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ደረጄ እንግዳ(ዶ/ር) የዩኒቨርስቲ መምህራን ለማህበረሰቡ አገልግሎት ስጡ ሲባሉ የውሸት ሪፖርት እንደሚያቀርቡና ይህም መስተካከል እንዳለበት ነግረውናል፡፡
ጅማ ዩኒቨርስቲ የመሰረቱትና መምህር የሆኑት ፕ/ር አስቻለው መንግስቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት ዩንቨርስቲዎች መካከል በማህበረሰብ አገልግሎት አሰጣጥ ጅማ ዩንቨርስቲ የተሻለ ነው ይላሉ፡፡
ለዚህም እንደ ምክንያት ያነሱት ዩንቨርስቲው ላለፉት 40 ዓመታት በሁሉም የትምህርት ክፍሎች የሚማሩ ተማሪዎችና መምህራን የማህበረሰብ አገልግሎት እንዲሰጡና ምርምር እንዲያደርጉ ስላስቻሉ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የዩኒቨርስቲዎች እና የማህበረሰብ ጉድኝት መላላትና በሁሉም ቦታ ወጥ አለመሆኑ ዋነኛ ችግር ያለው የቁጥጥር መላላት እና ትኩረት አለመስጠት መሆኑን የተናገሩት የኮተቤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ብርሃነ መስቀል ጠና(ዶ/ር) ናቸው፡፡
ማህበረሰቡም ቢሆን የዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አገልግሎት ለመስጠት ሴሄድ እምብዛም ፈቃደኝነት ያማያሳይበት ጊዜ አለ የሚሉት መሁራን ከዚህ ባለፈም አብሮ ከመስራት ይልቅ እርዳታን ብቻ የሚሻበት ጊዜ መኖሩን ያስረዳሉ፡፡
የተሻለ የትምህርት ጥራት ለመስጠትና የማህበረሰቡን ችግር የሚረዳ ትውልድ ማፍራት ከተፈለገ ይህ አገልግሎት ተግባራዊ ማድረግ ለነገ የማይባል ስራ ነው ያሉት ዶክተር ደረጄ ይህንን በመረዳት የአዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ከማህበረሰቡ ጋር ቀርቦ ለመስራት እየሞከረ ነው ብለዋል፡፡
እንደ ሀገር የማህበረሰቡን ችግር የሚረዳ ተማሪ ለማፍራትና ስራ ፈጣሪ ወጣቶች ከከፍተኛ ትምህርት ቋማት እንዲወጡ ከተፈለግ ይህ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና የማህበረሰቡን ጉድኝት መስተካከል እንዳለበት ምሁራኑ አሳስበዋል፡፡
ይህ ከሆነ ተሻሉ የምርምር ስራዎችና ብቁ ዩኒቨርስቲዎች እንደሀገር እንዲኖሩና ተመራቂ ተማሪውም ማህበረሰቡን የሚያውቅ ትውልድ መሆን ይልላል ተብሏል፡፡
በረከት አካሉ
Comments