top of page

ሐምሌ 9፣ 2016 - በወላጆች ቅሬታ የተነሳበት የቱርኩ ‘’ማሪፍ ኢንተርናሽናል ት/ቤት’’ ጉዳይ

''የአንደኛ ክፍል ዓመታዊ  ክፍያ ከ250,000 ብር ወደ 19405 ዶላር ሲደመር ሌሎች ክፍያዎች 880 ዶላር (575,000 ብር አካባቢ) ተደርጎብናል'' የተማሪ ወላጆች


‘’ተገቢ የሆነ ጭማሪ አደርገናል’’ ማሪፍ ትምህርት ቤት


‘’ጭማሪው ሲደረግ ጭራሽ አላወቅንም፣ ያወያየንም የለም’’ ወላጆች


‘’ህጉን ጠብቀን ለማሳወቅ ሞክረናል፣ ያልመጡትን ምንም ላደርግላቸው አልችልም’’ ትምህርት ቤቱ


በአዲስ አበባ የሚገኘው የቱርኩ ‘’ማሪፍ ኢንተርናሽናል ት/ቤት’’ ለ2017 የትምህርት ዘመን የጨመረው የትምህርት ቤት ክፍያ የተማሪ ወላጆች እና ትምህርት ቤቱን አላግባባ ብሏል፡፡


በማሪፍ ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት የካ እና ሲኤምሲ ቅርንጫፍ ልጆቻቸውን የሚያስተምሩ ወላጅ እንደሚሉት ት/ቤቱ ለሶስተኛ ተከታታይ ዓመት ለ2017 የትምህርት ዘመንም ጭማሪ አድርጓል፡፡

ወላጆቹ ጭማሪ መደረጉን ያወቁት ለ2017 የትምህርት ዘመን ክፍያ ለመፈፀም በዚህ ዓመት ግንቦት ወር ወደ ምህርት ቤቱ በሄዱበት አጋጣሚ መሆኑንን ነግረውናል፡፡


"ጭማሪ ለማድረግ የትምህርት ዘመኑ ከመድረሱ ሶስት ወር አስቀድሞ፤ ከተማሪ ወላጆች ከ50 በመቶ በላይ በተገኙበት፣ የመንግስት ተወካይ ባሉበት ወይይይት ተደርጎ፣ ጭማሪ ለማድረግ ከስምምነት ላይ ከተደረሰ፤ ይህ ተፈርሞ ለመንግስት ሲገባ ነው።


ማሪፍ ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት ክፍያ የጨመረብን ግን ከዚህ ህጋዊ አካሄድ አንዱንም ሳይፈፅም ነው" የሚሉት የተማሪ ወላጅ፤ ‘’ክፍያው የተጨማሪው እና ሳናውቅ፣ ሳንስማማ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ክፍያው የሚሰላው በውጭ ምንዛሬ እንዲሆን ተደርጎ ጭምር ነው’’ ሲሉ ወላጆች የደረሰባቸውን ቅሬታ በተመለከተ ለሸገር ተናግረዋል፡፡


‘’ቅሬታችንን መንግስት እንዲፈታልን ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ እስካሁን መፍትሄ አላመጣም’’ የሚሉት ወላጆች መንግስት "ተደራደሩ እና ተስማሙ" የሚል መልስ ወደ መስጠት አዘንብሏል ሲሉ መንግስትን በመፍትሄ አልሰጠንም ከሰዋል።


‘’እኛ መንግስት ያወጣውን ህግ ተከትሎ መፍትሔ እንዲሰጠን ብቻ ነው የምንፈልገው’’ ሲሉም ይጠይቃሉ።


‘’ምንም እንኳን ችግሩ መፍትሔ አስኪያገኝ የልጆቻችን ቦታ እንደሚጠበቅልን ቢነገረንም የተማሪዎች ምዝገባ ወቅት እያለቀ በመሆኑ ለልጆቻችን ሰግተናል’’ ብለዋል፡፡


ሸገር የተማሪ ወላጆቹን ቅሬታ ከሰማ በኋላ ትምህርት ቤቱን አነጋግሯል፡፡


በማሪፍ ት/ቤት ኢትዮጵያ የካምብሪጅ ካርኪውለም(Cambridge Curriculum) ዋና አስተባባሪ የሆኑትን አቶ ዮናስ ገደማን ሸገር ጠይቋል፡፡


አቶ ዮናስ ማሪፍ ኢንተርናሽናል ት/ቤት ለ2017 የትምህርት ዘመን የክፍያ ጭማሪ ማድረጉን ጠቅሰው ‘’ጭማሪ የተደረገው ግን ከተማሪ ወላጆች ጋር ተስማምተን፣ ህጉን ጠብቀን ለማሳወቅ ሞክረናል፣ በስብሰባ ላይ ያልተገኙትን ግን ምንም ማድረግ አንችልም’’ ብለዋል።


የተማሪ ወለጆች እኮ ትምህርት ቤቱ አላነጋገረንም፣ አልተስማማንም ብለዋል ያልናቸው አቶ ዮናስ ‘’እኛ ደግሞ ማወያየታችንን ነው ያልተገኘ ወላጅ ሊኖር ይችላል ያልነበሩትን በሂሳብ ክፍል እንዲያውቁት አድርገናል’’ ብለዋል።


ሌላው በማሪፍ ት/ቤት የቀረበው ቅሬታ ‘’ክፍያው በዶላር በእለቱ ምንዛሬ ተመን እንዲሆን ተደርጓል ይህ ደግሞ ከሀገሪቱ ህግ ውጪ ነው’’ የሚል ነው።


‘’የትምህርት ቤቱ ክፍያ በዶላር ምንዛሪ ተመን የተደረገው ትምህርት ቤቱ አለም አቀፍ ስለሆነ ሪፖርት የምናደርገው በዶላር ስለሆነ ለአሰራር እንዲያመች ነው ይህ ግን ቅሬታ በማስከተሉ እንዲቀር አድርገናል’’ ሲሉ የማሪፍ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ የካምብሪጅ ካርኪውለም ዋና አስተባባሪ አቶ ዮናስ ለሸገር ነግረዋል፡፡


በማሪፍ ኢንተርናሽናል ት/ቤት የ2017 የትምህርት ዘመን የክፍያ ጭማሪ ጉዳይ በተማሪ ወላጆች እና በትምህርት ቤቱ መካከል መግባባቱ ባለመቻሉ መፍትሄው ከመንግስት እየተጠበቀ ነው፡፡


ት/ቤቱም መንግስት መፍትሄ እንዲሰጥበት ውሳኔ እየጠበኩ ነው ብሏል፡፡


የትምህርት ስልጠና ጥራት ቁጥር ባለስልጣን በጉዳዩ ላይ በሁለት ቀናት ግፋ ቢል በሶስት ቀናት ውሳኔውን አሳውቃሁ ሲል ለሸገር ተናግሯል፡፡



ንጋቱ ሙሉ

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page