top of page

ሐምሌ 5፣2015 - አሳሳቢ የሆኑ የሰብአዊ መብት አያያዞች መቀጠላቸው ተነገረ

የሰሜኑ ጦርነት በሠላም ስምምነት መቋጨቱ የሀገሪቱን የሰብአዊ መብት አያያዝ ያሻሻለው ቢሆንም ወደኋላ የሚወስዱና አሳሳቢ የሆኑ የሰብአዊ መብት አያያዞች መቀጠላቸው ተነገረ፡፡


የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽኑ/ኢሰመኮ/ ከሰኔ 2014 ዓ.ም እስከ ሰኔ 2015 ዓ.ም ያለውን የሃገሪቱን የሰብአዊ መብት አያያዝ ሁኔታ የተመለከተ ሪፖርት ይፋ አድርጓል፡፡


ግጭቶች ፣ በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች የታጠቁ ቡድኖች እየተንቀሳቀሱ መሆኑ ለሰብአዊ መብት አያያዝ አሳሳቢ ተብለው በሪፖርቱ ተጠቅሰዋል፡፡


ዋና ኮሚሽነሩ ዶክተር ዳንኤል በቀለ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ዜጎችን አስገድዶ መወሰር ከሰወሩ በኋላም ማስፈራራት ማስቃየትና ባልታወቀ ቦታ እስከ ዓመት ድረስ ማቆየት እየጨመረ የመጣ የሰብአዊ መብት ጥሰት በዓመቱ አሳባቢ ከተባሉት መካከል ነው ብለዋል፡፡


ዜጎችን አስገድዶ መሰወር በተለይ በአዲስ አበባ ፣ በኦሮሚያና በአማራ ክልል መኖሩንና መቀጠሉንም ኮሚሽነሩ አንስተዋል፡፡


ከጎዳና ፣ ከቤታቸውና ከስራ ቦታቸው ተገደው በመንግስት የፀጥታ አካላት የተወሰዱ እና ከተሰወሩ ዜጎች መካከል ለዓመት ያህል ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ቤተሰብም የት እንዳሉ ሳያውቅ የቆዩ መኖራቸው ተነግሯል፡፡


ኢ-መደበኛ የሆኑ ማሰሪያ ቦታዎችም እየተበራከቱ ነው ያሉት ዶክተር ዳንኤል እንደ ምሳሌ በኦሮሚያ ክልል ተገደው የተሰወሩ ሰዎች በሸገር ከተማ ገላን አካባቢ በሚገኝ የቀድሞ የክልሉ ልዩ ሀይል ካምፕ የድብደባና የማሰቃየት ተግባር እንደሚፈፀምባቸው ጠቅሰዋል፡፡


ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሀገር ውስጥ ተፈናቃይ በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍል ያለ ሲሆን በቂ የእለት እርዳታ ካለማግኘታቸው ባሻገር ለመልሶ ማቋቋምና ለዘላቂ መፍትሄ ትርጉም ያለው ስራ አለመከወኑም አሳሳቢ ነው ተብሎ በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡


የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት አያያዝ እንዲሻሻል ተጎጂዎችን ማዕከል ያደረገ ፣ የሽግግር ፍትህ አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ጥበቃን ያማከለና አካታችነቱን ጠብቆ እንዲሄድ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ጠይቋል፡፡


በተጨማሪም በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች ካሉ የታጠቁ ሀይሎች ጋር መንግስት ችግሩን በሰላማዊ መንገድ በመፍታት ዘላቂ መፍትሄ እንዲሰጥ ተጠይቋል፡፡


ዓመቱ ከዚህ በፊት ያልነበሩ የሰብአዊ መብት ጥሰተቶች የተከሰቱበትም አመት ነበር የተባለ ሲሆን ወንጀሎችም መጠናቸው እና አሳሳቢነታቸው መጨመሩ የተነሳ ቢሆን መንግስት ትኩረት ሰጥቶ መፍትሄ እንዲሰጥ ተመክሯል፡፡ትዕግስት ዘሪሁን
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

Comments


bottom of page