top of page

ሐምሌ 4፣ 2016 - ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከዚህ በፊት በማይታወቁ የወባ በሽታ አምጭ ትንኞች የሚከሰት የወባ በሽታ እየጨመረ መምጣቱ ተነገረ

በኢትዮጵያ ካለፉት ቅርብ ዓመታት ወዲህ ከዚህ በፊት በማይታወቁ የወባ በሽታ አምጭ ትንኞች የሚከሰት የወባ በሽታ እየጨመረ መምጣቱ ተነገረ፡፡


የወባ በሽታ ስርጭቱ ቀንሶ የነበረ ቢሆንም፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ግን በወረርሽኝ ደረጃ እየተስፋፋ መሆኑ ተነግሯል፡፡


በሀገሪቱ ስርጭቱ እየሰፋ ያለውን የወባ በሽታ ለመከላል የወባ ትንኝ መከላከያ አጎበሮችን እና የመመርመሪያ ኪቶችን በማቅረብ ዩኤስኤአይዲ(USAID)ኢትዮጵያ ድጋፍ እያደረገ መሆኑ ተነግሯል፡፡


የወባ በሽታ መከላከሉ ላይ ካጋጠሙ ችግሮች ውስጥም ከዚህ ቀደም ያልነበሩ እና መድሃኒት የተላመዱ አዲስ ዝርያ የሆኑ የወባ አምጭ ትንኞች መከሰታቸውን የሚናገሩት በዩኤስኤአይዲ ኢትዮጵያ የጤና አገልግሎት ም/ዳይሬክተር የሆኑት ህሊና ወርቁ(ዶ/ር) ናቸው፡፡


ድርጅቱ በኢትዮጵያ ከሚከውናቸው የወባ መከላከል ስራዎች ውሰጥ የአጎበር ስርጭት እና የመመርመሪያ መሳሪያዎች እንደሚያቀርብና በዓመት 3 ሚሊየን የወባ መከላከያ አጎበር ለተለያዩ ክልሎች እንደሚሰራጭ ዶ/ር ህሊና ተናግረዋል፡፡


በጤና ሚኒስቴር የወባ እና ሌሎች ትንኝ ወለድ በሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ዴስክ ሃላፊው አቶ ጉዲሳ አሰፋ በበኩላቸው ባለፉት ዓመታት ወባን ለመከላከል የተከወኑ ስራዎች ውጤት የነበራቸው ቢሆንም በሀገሪቱ የተከሰቱ ግጭቶች እንዲሁም የኮቪድ ወረርሽኝ ለወባ ስርጭቱ መጨመር ምክንያት ሆነዋል ብለዋል፡፡


በጨማሪም የአየር ንብረት ለውጡን ተከትሎ ቀደም ሲል የተጠቀሰው አዲስ እንዲሁም መድኃኒት የተላመዱ የወባ አምጪ ትንኞች መከሰታቸው የበሽታ መከላከል ስራው ላይ ተጽዕኖ እንዳሳረፈ ተናግረዋል፡፡


በኢትዮጵያ የሚፈጠሩ ተደጋጋሚ ግጭቶች በሽታውን ለመከላከል እና ስርጭቱን ለመቀነስ የሚሰሩ ሥራዎችን እያደናቀፉ ነው ተብሏል፡፡


ከኢትዮጵያ አንድ ሚሊየን ስኩዌር ስፋት ውስጥ 75 በመቶ የሚሆነው ቦታ በእነዚህ አካባቢ ከሚኖሩት ውስጥ ደግሞ 69 በመቶ የሚሆነው የኅብረተሰብ ክፍል ለወባ በሽታ ተጋላጭ መሆኑን ሰምተናል፡፡


ምህረት ስዩምComments


bottom of page