በኢትዮጵያ በተከሰቱ ግጭቶች ሰዎች ተገድለዋል፣ አካላቸውን አጥተዋል፣ ለዘመናት ከኖሩበት ቤት ተፈናቅለዋል፣ ቤት ንብረታቸውን ጨምሮ የሚወዱትን ተነጥቀዋል፡፡
ለእነዚህ የተለያየ ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች የተለያዩ የግል እና የመንግስት ተቋማተ ድጋፍ አድርገናል ሲሉ ይሰማል፡፡
አብዛኛውም ጊዜ ለእነዚህ ሰዎች ተደረገላቸው የሚባለው ድጋፍ ደግሞ ቁሳዊ ነው፡፡
ነግር ግን ተጎጊጂዎቹ የአዕምሮ ቁስለትና የስነልቦና ጉዳት እንደሚደርስባቸው ባለሞያዎች ያስረዳሉ፡፡
ለዚህም ከቁሳዊ ድጋፍ ባልተናነሰ መልኩ በብዙ ነገር የተጎዳውን ስነልቦናቸውንም ማከም እንደሚያስፈልግ ይመክራሉ፡፡
አንድ በግጭት የተነሳ፤ እናት አባቱን ያጣ፣ ልጅ ቤተሰብ ውዳጁ የተገደለበት፣ ለዓመታት የኖረበት ቤት የተቃጠለበት፣ በአጠቃላይ ሞራሉን ጨምሮ የመኖር ተስፋውን ድንገት የተነጠቀ ሰው፤ ቁሳዊ ድጋፍ ቢደረግለትስ እንደ ቀድሞ ህይወቱን መቀጠል ይችላልን?

የስነልቦና ባለሞያ እና የፍካት የስነልቦና ማማከር አገልግሎት መስራች ኤርሚያስ ኪሮስ፤ ሰዎች ድንገት አሰቃቂ የሆነ ጉዳት በራሳቸውም ሆነ በሚወዱት ላይ ሲደርስባቸው፤ ክል አካል እንደሚታከም ሁሉ ስነልቦናቸውም መታከም እንደሚገባ ይናገራሉ፡፡
ይህ ሳያስቡት ድንገት የሚደርስባቸው ጉዳት፤ በነገሮች ላይ ያላቸውን እምነት ጭምር እንዲያጡ ከማድረጉም አልፎ በራስ የመተማመን ሞራላቸውና የወደፊት ተስፋቸውንም የማሳጣት እድሉ ሰፊ እንደሆነ የስነ ልቦና ባለሞያው ነግረውናል፡፡

በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ለሚገኙና እርዳታ ለሚሹ ሰዎች ድጋፍ ለማድረግ አላማ አድርገን ተቋቋምን የሚሉ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ቁጥራቸው ከ5000 በላይ ናቸው ተብሏል፡፡
ለመሆኑ እነዚህ ድጋፍ አድራጊ ድርጅቶች በስነልቦና የተጎዱ ሰዎችን ከማከም አንጻር እየሰሩት ያለው ስራ ምን ያህል ነው?
የሚሰሩትን ስራ የሚከታተልው የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣንን ጠይቀናል፡፡
በባለስልጣኑ የዋና ዳይሬክተር ጽ/ቤት ሀላፊ በፍቃዱ ወልደሰንበት በኢትዮጵያ በግጭትና በተለያዩ ምክንያቶች የስነ ልቦና ጉዳት እንደደረሰባቸው አስታውሰው፤ አብዛኛው እርጋታ የሚደረግላቸው ድግሞ ቁሳዊ ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ይህ ክፍተት መኖሩን ተገንዘበናል፤ ከአሁን በኋላ ከቁሳዊ በተጨማሪ የስነልቦናም ድጋፍ በእኛም በሌሎችም እንዲደረግ አቅደናል ሲሉም ነግረውናል፡፡
አቶ ሽብሩ ዲባ ጅረት የሰላምና እርቅ ድርጅት(JPRO) የተሰኘ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት የፕሮግራም ዳይሬክተር ሲሆኑ ተጎጂዎች ከቁሳዊ ድጋፍ ባለፈ ስለልቦናዊ ድጋፍ ማግኘት እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ እርዳታ ለማድረግ በሄድንባቸው ቦታዎችም የስነ-ልቦና ቁስለት የደረሰባቸው ሰዎችን አይተናል ብለውናል፡፡

በተመሳሳይ የአሜሪካን ፍሬንድስ ሰርቪስ ኮሚቴ(AFSC) የተሰኘ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት የአፍሪካ ቀንድ ሪሰርች እና ፖሊሲ ፕሮግራም አስተባባሪ የሆኑት አቶ ይሁን ብርሀነመስቀል በሀገሪቱ የስነልቦና ቁስል የገጠማቸው ብዙዎች እንደሆኑ መገንዘባቸውን አስታውሰው፤ ተጎጂዎቹን በተለያዩ መልኮች እየረዱ እንደሆነ ነግረውናል፡፡

ሌሎች አሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችም በስነልቦና እና በእርቅ ዙሪያ የተሻለ ግንዛቤ ኖሯቸው እንዲሰሩ በማለም ጄፕሮ እና ኤኤፍሲኤስ በመተባበር ስልጠናም እንደሰጡ ሰምተናል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን ከ4 ወር በፊት ባወጣው መረጃ መሰረት፤ የኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ቁጥር 4.4 ሚሊዮን ተሻግሯል፡፡
ማንያዘዋል ጌታሁን
ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ ይህንን ይጫኑ
Comments