በወላይታ ዞን በደረሰው የመሬት ናዳ የሟቾች ቁጥር 13 መድረሱ ተነገረ፡፡
የ6ቱ አስክሬን ገና በፍለጋ ላይ መሆኑን ዞኑ ለሸገር ተናግሯል፡፡
የወላይታ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ሳሙኦል ፎላ እንዳሉት አደጋው የደረሰው በክንደ ኮይሻ እና ካኦ ኮይሻ በተባሉ ሁለት ወረዳዎች ነው፡፡
በክንደ ኮይሻ 1 ሰው በመሬት ናዳው የሞተ ሲሆን በካኦ ኮይሻ 12 ሰው በናዳው ተቀብረው ህይወታቸው አልፏል ብለዋል፡፡
ከ12ቱ ማቾች መካከል አስከሬናቸው የተገኘው የ5ቱ ብቻ ሲሆን ቀሪዎቹ አስከሬኖች በናዳው ስለተቀበሩ በፍለጋ ላይ ነን ብለውናል አስተዳዳሪው፡፡
ትናንት ረፋድ ላይ በወላይታ ዞን በደረሰው የመሬት ናዳ የሟቾቹን አስከሬን ለማውጣት በሰው ሃይል ቁፋሮ እየተካሄደ ቀጥሏል፡፡
የመሬት ናዳው በደረሰባቸው ወረዳዎች ይኖሩ የነበሩ አንድ መቶ አባወራዎች የክረምት ጊዜው እስከሚያልፍ ድረስ ከአካባቢው እንዲነሱ ተደርገዋል የተባለ ሲሆን አሁን ያለው ችግር ከዞኑ አቅም በላይ አይደለም ሲሉም የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ሳሙኤል ነግረውናል፡፡
አሁንም ስጋት ያለባቸው 5 ወረዳዎች ተለይተው ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው የሚሉት አቶ ሳሙኤል ነዋሪውን ወደ ሌላ ስፍራ ወስዶ ለማስፈር የመሬት እጥረት ችግር መኖሩን ያስረዳሉ፡፡
አሁን በተከሰተው የመሬት ናዳ ከሰው ሕይወት ባለፈም በንብረት ላይ ውድመት ደርሷል፤ ተጨማሪ አደጋ ከተፈጠረ በሚል ደግሞ መጠለያ ድንኳኖች እና ትምህርት ቤቶች ለመጠለያነት ዝግጁ እየተደረጉ ነው ተብሏል፡፡
በረከት አካሉ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… https://bit.ly/33KMCqz
Comments