ነሀሴ 1፣2016 - በእርዳታ ሰበብ የራሳቸውን ፖሊሲ ለማስፈፀም እና የሀገር ሉዓላዊነት የሚዳፈሩ ድርጅትችን እየተቆጣጠርኩ ነው ሲል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ተናገረ
- sheger1021fm
- Aug 7, 2024
- 1 min read
በእርዳታ ሰበብ የራሳቸውን ፖሊሲ ለማስፈፀም እና የሀገር ሉዓላዊነት የሚዳፈሩ ድርጅትችን እየተቆጣጠርኩ ነው ሲል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ተናገረ፡፡
በኢትዮጵያ በተለያየ ችግር መነሾነት ለእርዳታ የተዳረጉ ሰዎችን ለመርዳት በሚል በህጋዊነት ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ ሀገር በቀል እና የውጭ ድርጅቶች እንዳሉ ይታወቃል፡፡
በተለይም መሰረታቸው ውጭ ሀገራት ያደረጉት እርዳታ ሰጪ ድርጅቶች በእርዳታ ሰበብ፤ የራሳቸውን ፍላጎት ይዘው የሚመጡ ናቸው ሲባል ይሰማል፡፡
ድርጅቶቹ የመጡበትን ሀገራት ፖሊሲን በእጃዙር በኢትዮጵያ ለማስፈፀም ይጥራሉ፣ የሀገርን ሉዓላዊነት የመዳፈር ተግባራትም ላይ ይሰማራሉ ተብለው ይጠረጠራሉ፡፡

የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣንን እንደሚለው ከሆነ የሀገር ክብር የማይጠብቁ ተግባራት ላይ የሚሰማሩት ላይ እስከ መዝጋት የሚደርስ እርምጃ ይወስዳል፡፡
በባለስልጣኑ የዋና ደይሬክተር ፅ/ቤት ሀላፊ በፍቃዱ ወልደሰንበት እንደሚሉት ማንኛውም እርምጃ ከመወሰዱ በፊት ብርቱ ክትትል ይደረጋል ብለውናል፡፡
ለተመዘገቡበት አላም እንዲሰሩ በሚያስፈልጋቸው ላይ ባለስልጣኑ ድጋፍ እንደሚያደርግ ያነሱት አቶ በፍቃዱ እጃቸውን ከሌላ ነገር ላይ የሚያነካኩ ድርጅቶች መኖራቸውንም ይናገራሉ፡፡
ባለፈው ዓመት በእንዲህ አይነት ተግባር የተሰማሩ ጥቂት ድርጅቶች ከድርጊታቸው ባለመታቀባቸው ከሀገር እንዲወጡ ሆኗልም ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በአንዳንዶች ስለሚነሳባቸው ወቀሳን በተመለከተ፤ መሰረታቸውን ውጭ አድርገው በኢትዮጵያ በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅትነት ተመዘግበው እየተንቀሳቀሱ ከሚገኙት መካከል አንዱ የሆነውን የአሜሪካን ፍሬንድስ ሰርቪስ ኮሚቴ(AFSC) ድርጅትን ጠይቀናል፡፡

የድርጅቱ የአፍሪካ ቀንድ ሪሰርች እና ፖሊሲ ፕሮግራም አስተባባሪ የሆኑት አቶ ይሁን ብርሀነመስቀል ድርጅታቸው እርዳታ ከማድረስ ባሻገር ሌላ አላማ እንደማራምድና ለዚሀም እያንዳንዱ የሚሰሩት ስራ ከሀገር በቀል ድርጅቶች አማካኝነት በሚመጡላቸው ሃሳቦች እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡
ድርጅታቸው የአሜሪካ ሀገር መሰረተት ይኑረው እንጂ የሚያገኙት ገንዘብ ከተለያዩ ተባባሪ አካላት እንጂ ካሜሪካ መንግስት እንዳልሆን ጠቅሰዋል፡፡
ስለዚህም ምንም አይነት የውጭ ፖሊሲ የማስፈጸም ዓላማም የለንም ብለውናል፡፡
ማንያዘዋል ጌታሁን
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… https://bit.ly/33KMCqz
תגובות